ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 10
10
ስለ መንፈሳዊ የጦር ዕቃ
1ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ ጳውሎስ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ብርቅ ግን የምደፍራችሁ በክርስቶስ የዋህነትና ቸርነት እማልዳችኋለሁ፥ በፍቅራችሁ እታመናለሁና።#“በፍቅራችሁ እታመናለሁና” የሚለው በግሪኩ የለም። 2ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ እሠራለሁ፤ በሥጋዊ ሥርዐትም እንደምንኖር አድርገው በሚጠረጥሩን ሰዎች ላይ በድፍረት ለመናገር አስባለሁ፤ እናንተ ግን በዚህ ዓይነት ድፍረት እንድናገር እንዳታደርጉኝ እለምናችኋለሁ። 3በሥጋችንስ እንሄዳለን፤ ነገር ግን በእርሱው ሥርዐት የምንሄድና የምንዋጋ አይደለም። 4የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ጽኑ ምሽግን በሚያፈርስ በእግዚአብሔር ኀይል ነው እንጂ። 5ልብ ሁሉ ይማረክ ዘንድ ኅሊናም ለክርስቶስ ይገዛ ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ የሚታበየውንና ከፍ ከፍ የሚለውን እናፈርሳለን።#ግእዙ “... ያፈርሳል ...” ይላል። 6እናንተ ትእዛዝን በፈጸማችሁ ጊዜ የማይገዛውን ሁሉ እኛ ልንበቀለው ዝግጁዎች ነን።
7በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ፤ ማንም በክርስቶስ ያመነ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቍጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛም እንዲሁ ነንና። 8እናንተን ለማነጽ እንጂ፥ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ በሰጠን ሥልጣን እጅግ የተመካሁት መመካት ቢኖር አላፍርም። 9ነገር ግን በመልእክቶች የማስፈራራችሁ እንዳይመስላችሁ፥ ይህን ትምክሕቴን እተወዋለሁ። 10ከሰዎች መካከል “መልእክቶቹ ከባዶችና አስጨናቂዎች ናቸው፤ ሰውነቱ ግን ደካማ ነው፤ ነገሩም ተርታ ነው” የሚሉ አሉና። 11ነገር ግን ይህን ነገር የሚናገር ይህን ይወቅ፤ በሌለንበት ጊዜ በመልእክታችን እንደ ተገለጠው እንደ ቃላችን፥ ባለንበትም ጊዜ በሥራችን እንዲሁ ነን። 12እነርሱ ራሳቸውን በአሰቡትና በገመገሙት መጠን ራሳቸውን ከሚያመሰግኑት ሰዎች ጋር ራሳችንን ልንቈጥር፥ ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርም፤ እነርሱ ራሳቸውም የሚናገሩትን ትርጕሙን አያውቁትም። 13እኛስ ወደ እናንተ እስክንደርስ ድረስ እግዚአብሔር በወሰነልን ሕግና ሥርዐት እንጂ፥ ከዐቅማችን አልፈን እጅግ አንመካም። 14ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን፥ ራሳችንን የምናመሰግን አይደለምና፤ ነገር ግን የክርስቶስን ሕግ በማስተማር ወደ እናንተ ደርሰናል። 15እኛስ በማይገባ ሌላ በደከመበት አንመካም፤ ነገር ግን ሃይማኖታችሁ እንድትሰፋ፥ የተሠራችላችሁ ሕግም በእናንተ እንድትጸና ተስፋ እናደርጋለን። 16አብዝተንም እናስተምራችኋለን፤ ያንጊዜም መጠናችን ከሥራችን ጋር ከፍ ከፍ ይላል፤ እኛስ ቀና ባልሆነውና በማይገባው አንመካም። 17#ኤር. 9፥24። “የሚመካ ግን በእግዚአብሔር ይመካ።” 18እግዚአብሔር ያከበረው ብቻ ይከብራል እንጂ ራሱን የሚያከብር የተመረጠ አይደለም።
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2 10: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in