የሐዋርያት ሥራ 2
2
ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ
1 #
ዘሌ. 23፥15-21፤ ዘዳ. 16፥9-11። ኀምሳው ቀንም በተፈጸመ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድነት በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። 2ድንገትም እንደ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ የነበሩበትንም ቤት ሞላው። 3እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም ታዩአቸው፤ በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው። 4ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደ አደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ።
5ከሰማይ በታች ካሉ አሕዛብ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደጋግ የአይሁድ ሰዎች ነበሩ። 6ይህንም ቃል ሲናገሩ ሰምተው ሁሉም ደንግጠው ተሰበሰቡ፤ ሁሉም በየሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋልና የሚሉትን አጡ። 7ተገረሙ፤ አደነቁም፥ እንዲህም አሉ፥ “እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? 8እንግዲህ በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንዴት እንሰማቸዋለን? 9እኛ በተወለድንበት በጳርቴ፥ በሜድ፥ በኢላሜጤ፥ በሁለቱ ወንዞች መካከል፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስና በእስያ፥ 10በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብፅ፥ በሊብያ አውራጃ፥ በቀርኔን የምንኖር፥ ከሮሜም የመጣን አይሁድ፥ መጻተኞችም፥#“መጻተኛ” የሚለው ከአረሚነት ወደ ይሁዲነት የገቡ ማለትን ያሳያል። 11ከቀርጤስና ከዐረብም የመጣን፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ጌትነት በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።” 12ሁሉም ተገረሙ፤ የሚሉትንም አጡ፥ እርስ በርሳቸውም፥ “እንጃ! ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ። 13እኩሌቶቹ ግን “እነዚህስ ጉሽ ጠጅ ጠግበው ሰክረዋል” ብለው ሳቁባቸው።
የጴጥሮስ ምስክርነት
14ጴጥሮስም ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “እናንተ የአይሁድ ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ ይህን ዕወቁ፤ ቃሌንም ስሙ። 15ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና። 16ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። 17#ኢዩ. 2፥28-32። በኋለኛዪቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል እግዚአብሔር፦ ሥጋን በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁ ራእይን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ። 18በወንዶችና በሴቶች ባሮች ላይም ያንጊዜ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። 19በላይ በሰማይ ተአምራትን፥ በታች በምድርም ምልክቶችን፥ ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ። 20የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። 21የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስለ ገለጠው
22“እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ነገር ስሙ፤ እንደምታውቁት በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእጁ ባደረገው በከሃሊነቱ በተአምራቱና በድንቅ ሥራዎቹ እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ሰው የናዝሬቱን ኢየሱስን ስሙ። 23#ማቴ. 27፥35፤ ማር. 15፥24፤ ሉቃ. 23፥33፤ ዮሐ. 19፥18። እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት። 24#ማቴ. 28፥5-6፤ ማር. 16፥6፤ ሉቃ. 24፥5። እግዚአብሔር ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና። 25ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። 26ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ። 27ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና። 28#መዝ. 15፥8-11። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ።#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ደስታም ዘወትር በቀኜ ነው” የሚል ይጨምራል።
29“እናንተ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት ነገር እንደ ሞተ እንደ ተቀበረም፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደ አለ ገልጬ እንድነግራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን? 30#መዝ. 131፥11፤ 2ሳሙ. 7፥12-13። ነቢይ ስለ ነበረ፥ ከአብራኩም የተገኘውን በዙፋኑ እንዲያነግሥለት እግዚአብሔር መሐላን እንደ ማለለት ስለ ዐወቀ፥ 31ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፥ ሥጋዉም በመቃብር እንደማይቀር፥ ጥፋትንም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ። 32እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮቹ ነን። 33አሁን ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ገንዘብ አድርጎ ይህን ዛሬ የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። 34ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፥ ነገር ግን እርሱ አለ፦ ጌታ ጌታዬን አለው፦ በቀኜ ተቀመጥ። 35#መዝ. 109፥1። ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስክጥላቸው ድረስ። 36እንግዲህ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም መሢሕም እንዳደረገው በርግጥ ይወቁ።”
37ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተከፈተ፤ ጴጥሮስንና ወንድሞቹ ሐዋርያትንም፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሏቸው። 38ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ንስሓ ግቡ፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፤ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ። 39ተስፋዉ ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ እግዚአብሔር አምላካችንም ለሚጠራቸው ርቀው ለነበሩ ሁሉ ነውና።” 40ሌላም ብዙ ነገር ነገራቸው፤ “ከዚህ ከክፉ ዓለምም ነፍሳችሁን አድኑ” ብሎ መከራቸው።
የክርስቲያን ማኅበር ዕድገት
41ቃሉንም ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚችም ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ተጨመሩ። 42በሐዋርያት ትምህርትና በአንድነት ማዕድን በመባረክ፥ በጸሎትም ጸንተው ይኖሩ ነበር። 43ሰው ሁሉ ፈራቸው፤ በሐዋርያትም እጅ ብዙ ተአምራትና ድንቅ ሥራ ይደረግ ነበር። 44#የሐዋ. 4፥32-35። ያመኑትም ሁሉ በአንድነት ይኖሩ ነበር፤ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበር። 45መሬታቸውንና ጥሪታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ እንደሚያሻው ይሰጡ ነበር። 46ሁልጊዜም አንድ ልብ ሆነው በቤተ መቅደስ ያገለግሉ ነበር፤ በቤትም ኅብስትን ይቈርሱ ነበር፤ በደስታና በልብ ቅንንነትም ምግባቸውን ይመገቡ ነበር። 47እግዚአብሔርንም ያመሰግኑ ነበር፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ መወደድ ነበራቸው፤ እግዚአብሔርም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 2: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in