ኦሪት ዘዳግም 24
24
ስለ ጋብቻና ፍች የተሰጠ ሕግ
1“አንድ ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፤ ከቤቱም ይስደዳት። 2ከቤቱም ከወጣች በኋላ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ 3ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት ፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት፥ 4የሰደዳት የቀድሞ ባልዋ ከረከሰች በኋላ ደግሞ ያገባት ዘንድ አይገባውም፤ ያ በእግዚአብሔር የተጠላ ነውና፤ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር አታርክስ።
ልዩ ልዩ ሕግጋት
5“አዲስ ሚስትም ያገባ ሰው ወደ ጦርነት አይሂድ፤ ምንም ነገር አይጫኑበት፤ ነገር ግን አንድ ዓመት በቤቱ በፈቃዱ ይቀመጥ፤ የወሰዳትንም ሚስቱን ደስ ያሰኛት።
6“የሰውን ነፍስ እንደ መውሰድ ነውና ወፍጮ ወይም መጅ ስለ መያዣ ማንም አይውሰድ።
7“ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ ሰውን አፍኖ ሲሰርቅና ሲሸጥ ቢገኝ ያን የሰረቀውን ሰው ይግደሉት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከላችሁ አርቁ።
8“ስለ ለምጽ ደዌ ሌዋውያን ካህናት ያስተማሩህን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ያስተማሩአችሁን” ይላል። ሁሉ ፈጽመህ እንድትጠብቅ እንድታደርግም ተጠንቀቅ፤ እኔ ያዘዝኋቸውን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 9አምላክህ እግዚአብሔር ከግብፅ ባወጣችሁ ጊዜ በመንገድ ሳላችሁ በማርያም ላይ ያደረገውን ዐስብ።
10“ለባልንጀራህ ባበደርኸው ጊዜ መያዣውን ልትወስድ ወደ ቤቱ አትግባ። 11አንተ ግን በውጭ ቁም፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ወደ ውጭ ያውጣልህ። 12ያም ሰው ድሃ ቢሆን መያዣውን በአንተ ዘንድ አታሳድር። 13ለብሶት እንዲተኛ እንዲባርክህም ፀሐይ ሳይገባ መያዣውን ፈጽመህ መልስለት፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ምጽዋት#ዕብ. “ጽድቅ” ይላል። ይሆንልሃል።
14“ከወንድሞችህ ወይም በሀገርህ ውስጥ ከአሉት መጻተኞች ድሃና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ ደመወዙን አትከልክለው፤ 15ድሃ ነውና፥ ተስፋውም እርሱ ነውና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ፥ ኀጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው።
16“አባቶች ስለ ልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም ስለ አባቶቻቸው አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኀጢአቱ ይገደል።
17“የመጻተኛውንና የድሃ-አደጉን፥ የመበለቲቱንም ፍርድ አታጣምምባቸው፤ የመበለቲቱንም ልብስ ለመያዣ አትውሰድባት። 18አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ ዐስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።
19“የእርሻህን መከር ባጨድህ ጊዜ ነዶም ረስተህ በእርሻህ ብታስቀር፥ ትወስደው ዘንድ አትመለስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ፥ ለመጻተኛና ለድሃ-አደግ፥ ለመበለትም ተወው። 20የወይራህን ፍሬ በለቀምህ ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ላይ አጥርተህ ለመልቀም ዳግመኛ አትመለስ፤ ለመጻተኛና ለድሃ-አደግ፥ ለመበለትም ይሁን። 21የወይንህን ፍሬ በቈረጥህ ጊዜ ቃርሚያውን አትልቀመው፤ ለመጻተኛና ለድሃ-አደግ፥ ለመበለትም ይሁን። 22አንተም በግብፅ ሀገር መጻተኛ እንደ ነበርህ ዐስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 24: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in