ኦሪት ዘዳግም 33
33
ሙሴ ለመጨረሻ ጊዜ እስራኤልን መባረኩ
1የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ሳይሞት የእስራኤልን ልጆች የባረከባት በረከት ይህች ናት። 2እንዲህም አለ፦
“እግዚአብሔር ከሲና መጣ፤
በሴይርም ተገለጠልን፤
ከፋራን ተራራ፥
ከቃዴስ#ዕብ. “ከእእላፋት ቅዱሳኑ ...” ይላል። አእላፋት ጋር ፈጥኖ መጣ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር በቀኙ ነበሩ።
3ለሕዝቡም ራራላቸው፤
ቅዱሳን ሁሉ ከእጅህ በታች ናቸው፤
እነርሱም የአንተ ናቸው።
ቃሎችህንም ይቀበላሉ።
4ሙሴም ለያዕቆብ ማኅበር ርስት የሆነውን ሕግ አዘዘን።
5የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ጋር በተሰበሰቡ ጊዜ፥
አለቃ በተወዳጁ ዘንድ ይሆናል።
6ሮቤልን እፈልገዋለሁ፤ አይሙትብኝ፤
ቍጥሩም ብዙ ይሁን።
7የይሁዳም በረከት ይህች ናት፤
አቤቱ የይሁዳን ቃል ስማ፤
ወደ ሕዝቡም ይግባ፤
እጆቹም ይግዙ፤
በጠላቶቹ ላይ ረዳት ትሆነዋለህ።
8ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፥
ለሌዊ ቃሉን፥
በመከራም ለፈተኑት፥
በክርክር ውኃም ለሰደቡት፥
ለእውነተኛው ሰው ጽድቁን መልስ።
9እናቱንና አባቱን አላየኋችሁም ላለ፥
ወንድሞቹንም ላላወቀ፥
ልጆቹንም ላላስተዋለ፤
ቃልህን ለጠበቀ፥
በቃል ኪዳንህም ለተማጠነ።
10ፍርድህን ለያዕቆብ፥
ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራሉ፤
በማዕጠንትህ ዕጣንን፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በቍጣህ ጊዜ ዕጣንን” ይላል።
በመሠዊያህም የሚቃጠል መሥዋዕትን ሁልጊዜ ያቀርባሉ።
11አቤቱ ኀይሉን ባርክ፤
የእጁንም ሥራ ተቀበል፤
በሚቃወሙት ጠላቶቹ ላይ መከራን አውርድ፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሚነሣበትን ወገብ ውጋው” ይላል።
የሚጠሉትም አይነሡ።
12ስለ ብንያምም እንዲህ አለ፦
በእግዚአብሔር የተወደደ በእርሱ ዘንድ ተማምኖ ይኖራል፤
እግዚአብሔርም በዘመኑ ሁሉ ይጋርደዋል፤
በትከሻውም መካከል ያድራል።
13ስለ ዮሴፍም እንዲህ አለ፦
ምድሩ ከእግዚአብሔር በረከት፥
ከሰማይ ዝናምና ጠል፥
ከታችም ከጥልቁ ምንጭ ናት።
14ከፀሐይ መውጣት ከሚገኘው ፍሬ፥
በወራት ቍጥር ከሚገኘው ምርት፥
15ከቀደሙትም ተራሮች ከፍተኛነት፥
ከዘለዓለሙ ኮረብቶች ራሶች፥
16በየወቅቱም ከምድሪቱ ምላት፥
በቍጥቋጦው ውስጥ ከነበረው በረከት፥
በዮሴፍ ራስ ላይ፥
ከወንድሞቹም በከበረው በእርሱ ራስ ላይ ይውረድ።
17ውበቱ እንደ ላም በኵር ነው፤
ቀንዶቹ አንድ ቀንድ እንዳለው ናቸው፤
በእነርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይወጋል፤
የኤፍሬም እልፍ አእላፋት፥
የምናሴም አእላፋት እነርሱ ናቸው።
18ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ፦
ዛብሎን ሆይ፥ በመውጣትህ፥
ይሳኮር ሆይ፥ በድንኳንህ ውስጥ ደስ ይበላችሁ።
19አሕዛብን ያጠፉአቸዋል፤
በዚያም ይጠሩአቸዋል፤
የጽድቅ መሥዋዕትንም ይሠዋሉ፤
የባሕሩም ሀብት፥
በባሕሩ ዳር የሚኖሩ ሰዎችም ገንዘብ ይመግብሃልና፥
20ስለ ጋድም እንዲህ አለ፦
ጋድን ሰፊ ያደረገ ቡሩክ ይሁን፤
እንደ አንበሳ ያለቆችን ክንድ ቀጥቅጦ ያርፋል።
21በዚያ ከሕዝቡ ገዦች ጋር የተሰበሰቡ የአለቆች ምድር እንደ ተከፈለች፥
የመጀመሪያውን ፍሬ አየ፤
እግዚአብሔርም ጽድቁን፥
ፍርዱንም ከእስራኤል ጋር አደረገ።
22ስለ ዳንም እንዲህ አለ፦
ዳን የአንበሳ ደቦል ነው፤
ከባሳን ይበርራል።
23ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦
ንፍታሌም ከበጎ ነገር ጠግቦአል፤
የእግዚአብሔርንም በረከት ተሞልቶአል፤
ባሕርንና ሊባን ይወርሳል።
24ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦
አሴር ከልጆች የተነሣ የተባረከ ይሁን፤
ለወንድሞቹም የተመረጠ ይሁን፤
እግሩንም በዘይት ያጥባል።
25ጫማህ ብረትና ናስ ይሆናል፤
እንደ ዕድሜህ እንዲሁ ኀይልህ ይሆናል።
26እንደ ፍቁሩ አምላክ ማንም የለም፤
በሰማይ የሚኖረው፥ በጠፈርም በታላቅነት ያለው እርሱ ረዳትህ ነው።
27እግዚአብሔርም ፊት ለፊት፥
በዘለዓለም ክንዶች ኀይል ይጋርድሃል፤
ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦
አጥፋው ይላል።
28እስራኤልም ተማምኖ፥
በያዕቆብ ምድር ብቻውን፥
በስንዴና በወይን ምድር ይኖራል፤
ሰማይ ከደመናና ከጠል ጋር ለአንተ ነው።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰማይ ጠልን ለአንተ ይሰጣል” ይላል።
29እስራኤል ሆይ ብፁዕ ነህ፤
በእግዚአብሔር የዳነ ሕዝብ እንደ አንተ ማንነው?
እርሱ ያጸንሃል፤ ይረዳሃልም፤
ትምክሕትህ በሰይፍህ ነው፤
ጠላቶችህ ውሸታሞች ናቸው፤
አንተም በአንገታቸው ላይ ትጫናለህ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 33: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in