ኦሪት ዘዳግም 7
7
ከአሕዛብ ስለ መለየት
(ዘፀ. 34፥11-16)
1“አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙና ታላላቅ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን፥ የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጤዎናዊውን፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ከነዓናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ 2አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና በመታሃቸው ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፤ አትማራቸውም፤ 3ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። 4ልጅህን ከእኔ ያርቀዋልና፤ ሌሎችን አማልክትም ያመልካልና። የእግዚአብሔርም ቍጣ ይነድድባችኋል፤ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። 5ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የአማልክቶቻቸውንም ምስል በእሳት አቃጥሉ።
6“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ርስት” ይላል። ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና። 7እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ፥ ከአሕዛብ ሁሉ ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንት ከአሕዛብ ሁሉ ጥቂቶች ነበራችሁና፤ 8ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ፥ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ፥ በተዘረጋችም ክንድ አወጣችሁ፤ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። 9አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም፥ ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ ዕወቅ፤ 10የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፤ ነገር ግን በፊቱ ብድራትን ይመልስበታል። 11እንግዲህ ታደርጓት ዘንድ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዐት፥ ፍርድንም ጠብቁ።
ለእግዚአብሔር መታዘዝ የሚያስገኘው በረከት
(ዘዳ. 28፥11-14)
12“እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምታችሁ ብትጠብቋት፥ ብታደርጓትም፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለእናንተ ይጠብቅላችኋል፤ 13ይወድድህማል፤ ይባርክህማል፤ ያባዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ፥ የመሬትህንም ፍሬ፥ እህልህን፥ ወይንህንም፥ ዘይትህንም፥ የከብትህንም ብዛት፥ የበግህንም መንጋ ይባርክልሃል። 14ከአሕዛብም ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፤ ከሴቶችህ መካን አትኖርም፤ ልጆች የሌሏት አገልጋይም አትኖርም፤ ከከብትህም መካን አይኖርም።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “በሰውህና በከብትህ ዘንድ የወንድ ወይም የሴት መካን አይኖርም” ይላል። 15በግብፃውያን ላይ ሲመጣ ያየኸውን ክፉ ሕማምና ደዌ ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ያርቅልሃል፤ ያየኸውንም መከራ ሁሉ ወደ አንተ አያመጣውም፤ ከአንተም በሚጠሉህ ሁሉ ላይ ይመልሰዋል። 16አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የአሕዛብ ምርኮ ትበላለህ፤ ዐይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ለአንተ ክፉ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው።
17“በልብህም፦ እነዚህ አሕዛብ ከእኔ ይልቅ ይበዛሉና አወጣቸው ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብለህ፥ አትፍራቸው፤ 18ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ሁሉ ያደረገውን ፈጽመህ አስብ፤ 19አምላክህ እግዚአብሔር ዓይንህ እያየች፥ ታላቅ መቅሠፍትን፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ የጸናችውንም እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። 20ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት፥ ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ መቅሠፍትን ይልክባቸዋል። 21ከፊታቸው አትደንግጥ፤ አምላክህ እግዚአብሔር፥ ከአንተ ጋር ነውና፥ እርሱም አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና ጽኑዕ ነውና። 22አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ ምድርም ምድረ በዳ እንዳትሆን#“ምድር ምድረ በዳ እንዳትሆን” የሚለው በዕብ. የለም። የምድረ በዳ አራዊትም እንዳይበዙብህ ፈጥኜ አጠፋቸዋለሁ አትበል። 23አምላክህ እግዚአብሔር ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ውርደት ይደመስሳቸዋል። 24ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ ስማቸውንም ከዚያ ቦታ ያጠፋል፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም ከፊትህ ይቆም ዘንድ አይችልም። 25የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ ከእነርሱም የተሠራባቸውን ብርንና ወርቅን፥ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትበድልበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። 26ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ እንደ እርሱም ርጉም ትሆናለህ፤ ርጉም ነውና መጸየፍን ተጸየፈው፤ መጥላትንም ጥላው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 7: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in