ትንቢተ ኢሳይያስ 55
55
የእግዚአብሔር ምሕረት
1እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ሂዱ፤ ገንዘብም የሌላችሁ ሂዱና ግዙ፤ ብሉ፤ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ጠጡ። 2ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፤ በረከትንም ብሉ፤ ሰውነታችሁም በበረከት ደስ ይበለው። 3ስሙኝ፤ ጎዳናዬን ተከተሉ፤ አድምጡኝም፤ ሰውነታችሁም በበረከት ትኖራለች፤ የታመነችዪቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘለዓለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። 4እነሆ፥ ለአሕዛብ ምስክር፥ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን አደረግሁት። 5እነሆ፥ የማያውቁህ ሕዝብ ይጠሩሃል፤ የእስራኤል ቅዱስ አክብሮሃልና ስለ አምላክህ ስለ እግዚአብሔር የማያውቁህ ሕዝብ በአንተ ይማጠናሉ።
6እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ 7ክፉ ሰው መንገዱን፥ በደለኛም ዐሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ፤ እርሱም ይምረዋል፤ እርሱ ብዙ በደላችሁን ይተውላችኋልና። 8ዐሳቤ እንደ ዐሳባችሁ፥ መንገዴም እንደ መንገዳችሁ አይደለምና፥ ይላል እግዚአብሔር። 9ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ፥ ዐሳቤም ከዐሳባችሁ የራቀ ነው። 10ብዙ ዝናምና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፥ ምድርን እንደሚያረካት፥ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፥ ዘርን ለሚዘራ፥ እህልንም ለምግብ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፥ 11ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ነው፤ የምሻውን እስኪያደርግ ድረስ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም፤ መንገዴንና ትእዛዜን አከናውናለሁ። 12እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሐሤትም ትማራላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በደስታ ሊቀበሏችሁ ይዘላሉ፤ የሜዳም ዛፎች ሁሉ በቅርንጫፎቻቸው ያጨበጭባሉ። 13በእሾህም ፋንታ ጥድ፥ በኵርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል፤ የእግዚአብሔርም ስም ለዘለዓለም በማይጠፋ ምልክት ይመሰገናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 55: አማ2000
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in