YouVersion Logo
Search Icon

የያ​ዕ​ቆብ መል​እ​ክት 3

3
አንደበትን ስለ መቈጣጠር
1ወንድሞቼ ሆይ! ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፤ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። 2ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው። 3እነሆ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፤ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። 4እነሆ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። 5እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ የአካል ክፍል ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። 6አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በሰውነታችን ክፍሎች መካከል ዐመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፤ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፤ በገሃነምም ይቃጠላል። 7የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፤ ደግሞ ተገርቶአል፤ 8ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም፤ የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። 9በእርሱ ጌታንና አብን እናመሰግናለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤ 10ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ። ወንድሞቼ ሆይ! ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም። 11ምንጭስ ከአንድ አፍ የሚጣፍጥንና የሚመርን ውሃ ያመነጫልን? 12ወንድሞቼ ሆይ! በለስ ወይራን ወይስ ወይን በለስን ልታፈራ ትችላለችን? ከጨው ውሃም ጣፋጭ ውሃ አይወጣም።
ሰማያዊ ጥበብ
13ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። 14ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ። 15ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፤ የሥጋም ነው፤ የአጋንንትም ነው፤ 16ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና። 17ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት። 18የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in