የዮሐንስ ወንጌል 13
13
ጌታ የደቀ መዛሙርቱን እግር እንደ አጠበ
1ከፋሲካ በዓል አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ወደ ላከው ወደ አብ ይሄድ ዘንድ ጊዜው እንደ ደረሰ ባወቀ ጊዜ በዓለም ያሉትን የወደዳቸውን ወገኖቹን ፈጽሞ ወደዳቸው። 2ራት ሲበሉም አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ሰው በይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ። 3ጌታችን ኢየሱስም፥ አብ ሁሉን በእጁ እንደ ሰጠው፥ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ባወቀ ጊዜ፥ 4ራት ከሚበሉበት ተነሥቶ ልብሱን አኖረና ማበሻ ጨርቅ አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ። 5በኵስኵስቱም ውኃ ቀድቶ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ጀመር፤ በዚያ በታጠቀው ማበሻ ጨርቅም አበሰ። 6ወደ ስምዖን ጴጥሮስም ደረሰ፤ እርሱም፥ “አቤቱ፥ አንተ እግሬን ታጥበኛለህን?” አለው። 7ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፤ ኋላ ግን ታስተውለዋለህ” ብሎ መለሰለት። 8ጴጥሮስም፥ “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም” ብሎ መለሰለት። 9ስምዖን ጴጥሮስም፥ “አቤቱ፥ እንኪያስ የምታጥበኝ እጆችንና ራሴንም እንጂ እግሮችን ብቻ አይደለም፤” አለው። 10ጌታችን ኢየሱስም፥ “ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤ እናንተማ ንጹሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም” አለው። 11ጌታችን ኢየሱስም አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና ስለዚህ “ሁላችሁ ንጹሓን አይደላችሁም” አለ።
ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ቃል
12እግራቸውንም ካጠባቸው በኋላ ልብሱን አንሥቶ ለበሰና እንደ ገና ከእነርሱ ጋር ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፥ “ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን? 13እናንተ ‘መምህራችን፥ ጌታችንም’ ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። 14እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል።#በግሪኩ “እርስ በርሳችሁ ልትተጣጠቡ ይገባችኋል” ይላል። 15#ሉቃ. 22፥27። እኔ እንደ አደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። 16#ማቴ. 10፥24፤ ሉቃ. 6፥40፤ ዮሐ. 15፥20። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው የሚበልጥ መልእክተኛም የለም። 17ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ። 18#መዝ. 40፥9። ነገር ግን ይህን የምናገር ስለ ሁላችሁ አይደለም፤ የመረጥኋቸው እነማን እንደ ሆኑ እኔ አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚመገብ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሣ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። 19በሆነም ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ ከመሆኑ አስቀድሞ እነግራችኋለሁ። 20#ማቴ. 10፥40፤ ማር. 9፥37፤ ሉቃ. 9፥48፤ 10፥16። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”
አሳልፎ የሚሰጠውን ስለ ማመልከቱ
21ይህንም ተናግሮ ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ መሰከረ፤ እንዲህም አለ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል።” 22ደቀ መዛሙርቱም ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ተጠራጥረው እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ 23ጌታችን ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በጌታችን ኢየሱስ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። 24ስምዖን ጴጥሮስም እርሱን ጠቀሰና፥ “ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ጠይቀህ ንገረን” አለው። 25ያም ደቀ መዝሙር በጌታችን ኢየሱስ አጠገብ ቀረብ ብሎ፥ “ጌታ ሆይ፥ እርሱ ማነው?” አለው። 26ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህ እኔ እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የምሰጠው ነው” አለው፤ ያን ጊዜም እንጀራ በወጥ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮታዊው ይሁዳ ሰጠው። 27እንጀራውንም ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ በይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረበት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንግዲህ የምታደርገውን ፈጥነህ አድርግ” አለው። 28አብረውትም በማዕድ የተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው አላወቁም። 29ሙዳየ ምጽዋቱ በይሁዳ ዘንድ ነበረና፥ ለበዓል የምንሻውን ወይም ለነዳያን የምንሰጠውን ግዛ#በግሪኩ “... ለበዓል የምንሻውን ግዛ ወይም ለነዳያን ስጥ ያለው የመሰላቸው ነበሩ” ይላል። ያለው የመሰላቸው ነበሩ። 30ይሁዳም ያን እንጀራ ተቀብሎ ወዲያውኑ ወጣ፥ ሌሊትም ነበር።።
ከራት በኋላ የተነገረ
31ይሁዳም ከወጣ በኋላ ያንጊዜ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ከበረ። 32እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፥ ያንጊዜም ያከብረዋል። 33#ዮሐ. 7፥34። ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር አለሁ፤ ትሹኛላችሁ፤ ለአይሁድም እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁንም ለእናንተ እነግራችኋለሁ።
ስለ አዲስ ትእዛዝ
34 #
ዮሐ. 15፥12፤ 17፤ 1ዮሐ. 3፥23፤ 2ዮሐ. 5። “እርስ በርሳችሁ ቷደዱ ዘንድ፥ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። 35እርስ በርሳችሁም ብቷደዱ፥ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ሁሉ ያውቋችኋል።”
ጌታ ጴጥሮስ እንደሚክድ ስለ መናገሩ
36ስምዖን ጴጥሮስም፥ “ጌታ ሆይ፥ ወዴት ትሄዳለህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ ኋላ ግን ትከተለኛለህ” አለው። 37ጴጥሮስም፥ “ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ነፍሴንም እንኳ ቢሆን ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው። 38ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ነፍስህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ዶሮ አይጮህም።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 13: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in