የዮሐንስ ወንጌል 16
16
በሃይማኖት ስለ መጽናት
1“እንዳትሰናከሉ ይህን ነገርኋችሁ። 2ከምኵራባቸው ያስወጡአችኋል፤ ደግሞም እናንተን የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚያቀርብ የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንም፥ እኔንም ስላላወቁ ነው። 4ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ነገርኋችሁ። አስቀድሜ ግን ይህን አልነገርክኋችሁም ነበር፤ ከእናንተ ጋር ነበርሁና። 5አሁን ግን ወደ ላከኝ ወደ አብ እሄዳለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እንኳ፦ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ አይጠይቀኝም። 6ነገር ግን ይህን ስለ ነገርኋችሁ በልባችሁ ኀዘን ሞላ።
መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ተስፋ ስለመስጠቱ
7“እኔ በእውነት የሚሆነውን እነግራችኋለሁ፤ እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፤ እኔ ካልሄድሁ ጰራቅሊጦስ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ከሄድሁ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8እርሱም በመጣ ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአትና ስለ ጽድቅ፥ ስለ ፍርድም ይዘልፈዋል። 9ስለ ኀጢኣት፥ በእኔ አላመኑምና ነው፤ 10ስለ ጽድቅ፥ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፥ እንግዲህ ወዲህም አታዩኝምና ነው። 11ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዢ ይፈረድበታልና ነው።
12“የምነግራችሁ ብዙ ነገር ነበረኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። 13ያ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ እርሱ ከራሱ አይናገርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። 14እርሱም እኔን ያከብረኛል፤ ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋልና። 15ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህም ከእኔ ወስዶ ይነግራችኋል አልኋችሁ።
16“ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፤ ወደ አብ እሄዳለሁና።” 17ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ፥ ወደ አብ እሄዳለሁና የሚለን ይህ ነገር ምንድነው?” ተባባሉ። 18“ይህ ጥቂት የሚለን ምንድነው? የሚናገረውን አናውቅም” አሉ። 19ጌታችን ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደሚሹ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፥ “ጥቂት ጊዜ አለ፤ አታዩኝምም፤ ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንደገናም ታዩኛላችሁ” ስለ አልኋችሁ፥ ስለዚህ ነገር እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን?
ስለ ኀዘንና ስለ ደስታ
20“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፤ ዓለምም ደስ ይለዋል፤ እናንተ ግን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21ሴት በምትወልድበት ጊዜ ወራቷ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ነገር ግን ልጅዋን ከወለደች በኋላ ስለ ደስታዋ ከዚያ ወዲያ ምጥዋን አታስበውም፤ በዓለም ወንድ ልጅን ወልዳለችና። 22እናንተም ዛሬ ታዝናላችሁ፤ እንደገናም አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። 23ያንጊዜም እኔን የምትለምኑኝ አንዳች የለም፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በስሜ አብን ብትለምኑት ሁሉን ይሰጣችኋል። 24እስካሁን ምንም በስሜ አልለመናችሁም፤ ደስታችሁ ፍጹም ይሆን ዘንድ ለምኑ፤ ታገኙማላችሁ።
ዓለምን ድል ስለ መንሣት
25“ዛሬስ በምሳሌ ነገርኋችሁ፤ ነገር ግን የአብን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ እንጂ ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል። 26ያንጊዜ በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እለምነዋለህ አልላችሁም፤ 27እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ፤ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስለ አመናችሁብኝ እርሱ ራሱ አብ ወድዷችኋልና። 28ከአብ ወጣሁ፤ ወደ ዓለምም መጣሁ፤ ዳግመኛም ዓለምን እተወዋለሁ፤ ወደ አብም እሄዳለሁ።”
29ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት፥ “እነሆ፥ ዛሬ ገልጠህ ትናገራለህ፤ ምንም በምሳሌ የተናገርኸው የለም። 30አሁን አንተ ሁሉን እንደምታውቅ፥ ማንም ሊነግርህ እንደማትሻ ዐወቅን፤ በዚህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እናምናለን።” 31ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አሁን ታምናላችሁን? 32እያንዳንዳችሁ በየቦታዉ የምትበታተኑበት፥ እኔንም ብቻዬን የምትተዉበት ጊዜ ይደርሳል፤ ደርሶአልም፤ እኔ ግን ብቻዬን አይደለሁም፤ አብ ከእኔ ጋር ነውና። 33በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኋችሁ፤ በዓለም ግን መከራን ትቀበላላችሁ፤ ነገር ግን ጽኑ፤ እኔ ዓለሙን ድል ነሥቼዋለሁና።”
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 16: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in