መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 9
9
የገባዖን ሰዎች ኢያሱን እንዳታለሉት
1እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በሜዳውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥት ሁሉ፥ ኬጤዎናዊዉ፥ አሞሬዎናዊዉም፥ ከነዓናዊዉም፥ ፌርዜዎናዊዉም፥ ኤዌዎናዊዉም፥ ኢያቡሴዎናዊዉም፥ ጌርጌሴዎናዊዉም ይህን በሰሙ ጊዜ፥ 2ኢያሱንና እስራኤልን ሁሉ ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ።
3በገባዖን የሚኖሩ ሰዎች ግን እግዚአብሔር#ዕብ. “ኢያሱ” ይላል። በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ 4እነርሱ ደግሞ ተንኰል አድርገው መጡ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፤ በትከሻቸውም#ዕብ. “በአህዮቻቸው” ይላል። ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ ረዋት ተሸከሙ። 5በእግራቸውም ያደረጉት ጫማ ያረጀና ማዘቢያው የተበጣጠሰ፥ ልብሳቸውም በላያቸው ያረጀ ነበረ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀ፥ የሻገተና የተበላሸ ነበረ። 6ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ጉባኤ ወደ ጌልገላ መጥተው ለኢያሱና ለእስራኤል ሁሉ፥ “ከሩቅ ሀገር መጥተናል፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ” አሉ። 7የእስራኤልም ልጆች ኤዌዎናውያንን፥ “ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደ ሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን?” አሉአቸው። 8ኢያሱንም፥ “እኛ ባሪያዎችህ ነን፤ ከሩቅ ሀገርም ነን”#“ከሩቅ ሀገርም ነን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አሉት። ኢያሱም፥ “እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?” አላቸው። 9እነርሱም አሉት፥ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ስም እጅግ ከራቀ ሀገር ባሪያዎችህ መጥተናል፤ ዝናውንም፥ በግብፃውያንም ያደረገውን ሁሉ፥ 10በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞሬዎን ነገሥት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን፥ በአስታሮትና በኤድራይን በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። 11ሽማግሌዎቻችንና የሀገራችን ሰዎች ሁሉ፦ ለመንገድ ስንቅ ያዙ፤ ልትገናኙአቸውም ሂዱ፦ እኛ ባሪያዎቻችሁ ነን፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ በሉአቸው አሉን። 12ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ያዝነው፤ አሁንም እነሆ፥ ደርቆአል፤ ሻግቶአልም። 13እነዚህም የጠጅ ረዋቶች አዲሶች ሳሉ ሞላንባቸው፤ እነሆም፥ አርጅተው ተቀድደዋል፤ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል።” 14አለቆችም ከስንቃቸው ወሰዱ፤ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም። 15ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፤ በሕይወት እንዲተዋቸውም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው።
16ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ከቅርብ እንደሆኑና በአጠገባቸው እንደሚኖሩ ሰሙ። 17የእስራኤልም ልጆች ተጕዘው በሦስተኛው ቀን#“በሦስተኛው ቀን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ወደ ከተሞቻቸው ደረሱ፤ ከተሞቻቸውም ገባዖን፥ ከፊራ፥ ብኤሮትና ኢያሪም ነበሩ። 18የማኅበሩም አለቆች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልገደሉአቸውም። ማኅበሩም ሁሉ በአለቆቹ ላይ አጕረመረሙ። 19አለቆቹም ሁሉ ለማኅበሩ ሁሉ፥ “በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ምለንላቸዋል፤ ስለዚህም እንነካቸው ዘንድ ምንም አንችልም። 20ስለማልንላቸው መሐላ ጥፋት እንዳይሆንብን ይህን አናድርግባቸው፤ በሕይወትም እንተዋቸው፤ እንግዛቸውም” አሉአቸው። 21አለቆቹም “አዳንናችሁ፤ ለማኅበሩም እንጨት ትቈርጡና ውኃ ትቀዱ ዘንድ መደብናችሁ” አሉአቸው። አለቆቹም እንዲሁ አዘዙአቸው።
22ኢያሱም ጠርቶ፥ “እናንተ በመካከላችን የምትኖሩ ስትሆኑ፦ ‘ከእናንተ እጅግ የራቅን ነን’ ብላችሁ ለምን አታለላችሁን? 23አሁንም የተረገማችሁ ሁኑ፤ ለእኔም፥ ለአምላኬም እንጨት ቈራጭ፥ ውኃም ቀጂ የሆነ ባሪያ ከእናንተ አይጠፋም” አላቸው። 24መልሰውም ኢያሱን፥ “እኛ ባሪያዎችህ#“እኛ ባሪያዎችህ” የሚለው በግእዝና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ምድሪቱን ሁሉ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ ያጠፋ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘ በእውነት ሰምተናል፤ ስለዚህም ከእናንተ የተነሣ ስለ ነፍሳችን እጅግ ፈራን፤ ይህንም ነገር አድርገናል፤ 25አሁንም እነሆ፥ በእጃችሁ ውስጥ ነን፤ እንደ ወደዳችሁና ደስ እንደሚላችሁ አድርጉብን” አሉት፤#ዕብ. “በእጅህ ውስጥ ነን ለዐይንህም መልካምና ቅን የመሰለውን ነገር አድርግብን አሉት” ይላል። 26ኢያሱም እንዲሁ አደረገባቸው፤ ከእስራኤልም ልጆች እጅ አዳናቸው፤ አልገደሉአቸውምም። 27በዚያም ቀን ኢያሱ እነርሱን ለማኅበሩና ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቈራጮችና ውኃ ቀጂዎች አደረጋቸው። ስለዚህም የገባዖን ሰዎች ለማኅበሩና ለእግዚአብሔር መሠዊያ፥ እግዚአብሔርም ለመረጠው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ እንጨት ቈራጮች፥ ውኃም ቀጂዎች ሆኑ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 9: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in