YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ምሳሌ 23

23
1በመኳንንት ማዕድ ለመብላት በተቀመጥህ ጊዜ፥
ያቀረቡልህን ፈጽመህ ዕወቅ፤
2በእጅህ ተቀበል፥
እንደዚህም ታዘጋጅ ዘንድ እንዳለህ ዕወቅ።
3ብትሳሳ ግን ምግቡን አትውደድ
እርሱ የሐሰት እንጀራ ነውና።
4አንተም ድሃ ስትሆን ከባለጠጋ ጋር አትወዳደር።
በዐሳብህም ራቅ።
5በእርሱ ላይ ዐይንህን ብታተኩር አታገኘውም፥
ለእርሱ የንስር ክንፍ ተዘጋጅቶለታልና።
ወደሚቆምበትም ቤት ይመለሳልና።
6ከስስታም ሰው ጋር አትመገብ፥
ምግቡንም አትመኝ፤
7ሣርን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ፀጕር” ይላል። እንደሚበላ ይበላል፥ ይጠጣልም፤
ወደ አንተም አታስገባው፥
ከእርሱ ጋርም እንጀራን አትብላ፥
ብላ፥ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።
8የበላኸውን ትተፋለህ፥
ያማረውንም ቃልህን ታጠፋለህ።
9በሰነፍ ጆሮ አንዳች አትናገር፥
የነገርህን ጥበብ እንዳይንቅብህ።
10አባቶችህ ያኖሩትን የድንበር ምልክት አታፍልስ፤
ወደ ድሃ አደጎች እርሻም አትግባ፤
11ታዳጊአቸው እግዚአብሔር ጽኑ ነውና፥
እርሱም ፍርዳቸውን ከአንተ ጋር ይፋረዳልና።
12ልብህን ለተግሣጽ ስጥ፥
ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል አዘጋጅ።
13ሕፃናትን ከመቅጣት ቸል አትበል፥
በበትር ብትመታቸው አይሞቱምና።
14አንተ በበትር ትመታቸዋለህ፥
ነፍሳቸውን ግን ከሞት ታድናለህ።
15ልጄ ሆይ፥ ልብህ ጠቢብ ይሁን
ልቤን ደግሞ ደስ ያሰኛል፤
16በከንፈሮችህ ቃሌ ብትኖር
ለከንፈሮቼ የቀኑ ይሆናሉ።
17ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤
ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤
18ብትጠብቃቸው ዘመድ ይሆኑሃል፥
ተስፋህም አትጠፋም።
19ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ጠቢብም ሁን፥
የልብህንም ዐሳብ አቅና።
20የወይን ጠጅ ጠጭ አትሁን፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በግብዣ ቤት ብዙ ጊዜ አትዘግይ” የሚል ይጨምራል።
ለሥጋም አትሳሳ
21ሰካራምና አመንዝራ ይደኸያል፥
እንቅልፋምም ሁሉ የተቦጫጨቀ ጨርቅ ይለብሳል።
22ልጄ ሆይ፥ የወለደህን አባትህን ስማ፥
እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት።
23እውነትን ግዛ፥ አትሽጣትም፥
ጥበብንና ተግሣጽን፥ ማስተዋልንም።#ከዕብራይስጥ የተወሰደ ነው።
24ጻድቅ አባት በመልካም ያሳድጋል፥
በብልህ ልጅም ነፍሱ ደስ ይላታል።
25አባትህና እናትህ በአንተ ደስ ይላቸዋል፥
አንተንም የወለደች ደስ ይላታል።
26ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥
ዐይኖችህም መንገዴን ይጠብቁ።
27አመንዝራ ሴት የተነደለች ማድጋ ናት፥
ሌላዪቱም ሴት የጠበበች ጕድጓድ ናት።
28ወደ እርሷ የሄደ ፈጥኖ ይጠፋል፥
ጠማማ ሰውም ሁሉ ያልቃል።
29ልጄ ሆይ፥ ዋይታ ለማን ነው?
ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው?
ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው?
የዐይን ቅላት ለማን ነው?
30የወይን ጠጅ በመጠጣት ለሚዘገዩ አይደለምን?
የወይንን ፍለጋ ለሚከተሉስ አይደለምን?
ግብዣ ከተደረገ ዘንድ በወይን አትስከሩ፥
ነገር ግን ከደጋግ ሰዎች ጋር በመደማመጥ ተነጋገሩ።
31ወደ ጽዋዎችና ወደ ብርሌ ዐይንህን ብትሰጥ፥
በኋላ እንደ ግንብ ዕራቁትህን ትሄዳለህ፤
32በመጨረሻም እባብ እንደ ነደፈው፥
የእፉኝትም መርዝ እንደ ተሰራጨበት ትዘረጋለህ።
33ዐይኖችህ ጋለሞታዎችን ያያሉ፥
ያንጊዜም አፍህ ጠማማ ነገርን ይናገራል።
34በጥልቅ ባሕር ውስጥ እንደሚተኛ ትሆናለህ፥
በብዙ ማዕበል ውስጥም እንደሚቀዝፍ።
35“መቱኝ፥ ያውም አልተሰማኝም፤
ዘበቱብኝ፥ እኔም አላወቅሁም።
ከእኔ ጋር የሚሄዱትን መጥቼ እፈልግ ዘንድ
መቼ ጧት ይሆናል?” ትላለህ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in