YouVersion Logo
Search Icon

የዮ​ሐ​ንስ ራእይ 1

1
መግቢያና ሰላምታ
1ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፤ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፤ 2እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ። 3ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።
4-5ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው፥ ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር፥ ከሙታንም በኵር፥ የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን፥ ከኀጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥ 6መንግሥትም፥ ለአባቱም ለእግዚአብሔር ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኀይል ይሁን፤ አሜን። 7እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዐይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፤ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፤ አሜን።
8ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ “አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ፤” ይላል።
የክርስቶስ በራዕይ መገለጥ
9እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ። 10በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፤ 11እንዲሁም “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊላደልፊያም ወደ ሎዲቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ፤” አለኝ።
12የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፤ 13በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 14ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ 15እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውሃዎች ድምፅ ነበረ። 16በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፤ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኀይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ።
17ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ፤ እንዲህም አለኝ “አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው እኔ ነኝ፤ 18ሕያውም እኔ ነኝ፤ ሞቼም ነበርሁ፤ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ። 19እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ። 20በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፤ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for የዮ​ሐ​ንስ ራእይ 1