YouVersion Logo
Search Icon

1 ወደ ጢሞቴዎስ 5

5
1-2ሽማግሌ የሆነውን አትገሥጸው፥ እርሱን ግን እንደ አባት፥ ጎበዞችን እንደ ወንድሞች፥ የሸመገሉትን ሴቶች እንደ እናቶች፥ ቆነጃጅቱን እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና ለምናቸው።
3በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። 4ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተ ሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። 5ብቻዋንም ኖራ በእውነት ባልቴት የምትሆን በእግዚአብሔር ተስፋ ታደርጋለች፥ ሌትና ቀንም በልመና በጸሎትም ጸንታ ትኖራለች፤ 6ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት። 7ያለ ነቀፋ እንዲሆኑ ይህን ደግሞ እዘዝ። 8ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።
9ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፥ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤ 10ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል። 11ባል የሞተባቸውን ቆነጃጅት ግን አትቀበል፤ በክርስቶስ ላይ ተነሥተው ሲቀማጠሉ ሊያገቡ ይወዳሉና፤ 12የፊተኛውንም እምነታቸውን ስለ ናቁ ይፈረድባቸዋል፤ 13ከዚህም ጋር ቤት ለቤት እየዞሩ ሥራን መፍታት ደግሞ ይማራሉ፥ የማይገባውንም እየተናገሩ ለፍላፊዎችና በነገር ገቢዎች ይሆናሉ እንጂ፥ ሥራ ፈቶች ብቻ አይደሉም። 14እንግዲህ ቆነጃጅት ሊያገቡ፥ ልጆችንም ሊወልዱ፥ ቤቶቻቸውንም ሊያስተዳድሩ፥ ተቃዋሚውም የሚሳደብበትን አንድን ምክንያት ስንኳ እንዳይሰጡ እፈቅዳለሁ፤ 15ከአሁን በፊት አንዳንዶች ሰይጣንን እንዲከተሉ ፈቀቅ ብለዋልና። 16ባልቴቶች ያሉት የሚያምን ቢሆን ወይም የምታምን ብትሆን፥ ይርዱአቸው፥ ቤተ ክርስቲያንም እውነተኞችን ባልቴቶች እንድትረዳ አይክበዱባት።
17በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። 18መጽሐፍ፦ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ፦ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና። 19ከሁለት ወይም ከሦስት ምስክር በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። 20ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሰሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው። 21አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ። 22በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፥ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ።
23ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ።
24የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤ 25እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፥ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in