YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘዳግም 4

4
1አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። 2እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም። 3ብዔልፎጎርን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በብዔልፎጎር ያደረገውን ዓይኖቻችሁ አይተዋል። 4እናንተ ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ ሁላችሁ በሕይወት ትኖራላችሁ። 5እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ ታደርጉ ዘንድ አምላኬ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ፍርድን አስተማርኋችሁ። 6ጠብቁአት አድርጉአትም፤ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው፦ በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና፤ 7አምላካችን እግዚአብሔር በምንጠራው ጊዜ ሁሉ እንደሚቀርበን፥ አምላኩ ወደ እርሱ የቀረበው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? 8በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንደማኖራት እንደዚህች ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ፍርድ ያለው ታላቅ ሕዝብ ማን ነው? 9-10እግዚአብሔር፦ ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ ልጆቻቸውንም ያስተምሩ ዘንድ ቃሌን አሰማቸዋለሁ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በኮሬብ በቆምህበት ቀን ዓይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይወድቅ ተጠንቀቅ፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አስታውቀው። 11እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር፤ እስከ ሰማይም መካከል ድረስ አሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር፤ ጨለማና ደመና ድቅድቅ ጨለማም ነበረ። 12እግዚአብሔርም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ የቃልን ድምፅ ሰማችሁ፥ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅን ብቻ ሰማችሁ። 13ታደርጉትም ዘንድ ያዘዛችሁን ቃል ኪዳን አሥሩን ቃላት ነገራችሁ፤ በሁለቱም በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። 14ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር የምታደርጉአትን ሥርዓትና ፍርድ አስተምራችሁ ዘንድ እግዚአብሔር በዚያን ጊዜ አዘዘኝ። 15እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ፤ 16እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥ 17በምድር ላይ ያለውን የእንስሳን ሁሉ ምሳሌ፥ በሰማይም በታች የሚበርረውን የወፍን ሁሉ ምሳሌ፥ 18በምድርም ላይ የሚሽከረከረውን ሁሉ ምሳሌ፥ ከምድርም በታች በውኃ ውስጥ የሚኖረውን የዓሣን ሁሉ ምሳሌ እንዳታደርጉ፥ 19ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰማይ ሁሉ በታች ላሉት አሕዛብ ሁሉ የሰጣቸውን ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንና የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባየህ ጊዜ፥ ሰግደህላቸው አምልከሃቸውም እንዳትስት ተጠንቀቅ። 20እናንተን ግን እንደ ዛሬው ሁሉ የርስቱ ሕዝብ ትሆኑለት ዘንድ እግዚአብሔር ወስዶ ከብረት እቶን ከግብፅ አወጣችሁ። 21እግዚአብሔርም በእናንተ ምክንያት ተቆጣኝ፥ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገር፥ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። 22እኔ ግን በዚህች ምድር እሞታለሁ፥ ዮርዳኖስንም አልሻገርም፤ እናንተ ግን ትሻገራላችሁ፥ ያችንም መልካሚቱን ምድር ትወርሳላችሁ። 23አምላካችሁም እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ፥ አምላክህም እግዚአብሔር የከለከለውን በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ። 24አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነውና። 25ልጆችን የልጅ ልጆችንም በወለዳችሁ ጊዜ፥ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ በረከሳችሁም ጊዜ፥ በማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል ባደረጋችሁ ጊዜ፥ ታስቆጡትም ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር በሠራችሁ ጊዜ፥ 26ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንድትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ አስመሰክራለሁ፤ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትቀመጡባትም። 27እግዚአብሔርም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ እግዚአብሔር በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ። 28በዚያም የማያዩትን የማይሰሙትንም የማይበሉትንም የማያሸቱትንም፥ በሰው እጅ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት ታመልካላችሁ። 29ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ። 30ይህም ሁሉ በደረስብህ ጊዜ፥ ስትጨነቅ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ትመለሳለህ፥ ቃሉንም ትሰማለህ። 31አምላክህ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተውህም፥ አያጠፋህምም፥ ለአባቶችህም የማለላቸውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም። 32እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቃ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። 33አንተ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ ሰማህ፥ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ በሕይወት ይኖራልን? 34አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን? 35እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። 36ያስተምርህ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማህ፤ በምድርም ላይ ታላቁን እሳት አሳየህ፤ ከእሳትም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። 37-38አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። 39እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ። 40ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ። 41-42በዚያን ጊዜ ሙሴ ትናንት ከትናንት በስቲያም ጠላቱ ያልሆነውን ባልንጀራውን ሳያውቅ የገደለ ገዳዩ ይሸሽባቸው ዘንድ፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት ይኖር ዘንድ በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ለየ። 43ከተሞቹም ለሮቤል ነገድ በምድረ በዳ በደልዳላ ስፍራ ያለ ቦሶር፥ ለጋድም ነገድ በገለዓድ ያለ ራሞት፥ ለምናሴም ነገድ በባሳን ያለ ጎላን ነበሩ። 44ሙሴም በእስራኤል ልጆች ፊት ያኖራት ሕግ ይህች ናት፤ 45-46ሙሴና የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ከወጡ በኋላ በመቱት፥ በሐሴቦን ተቀምጦ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፥ በቤተ ፌጎር አንጻር ባለው ሸለቆ በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከግብፅ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ምስክርና ሥርዓት ፍርድም ይህ ነው። 47የእርሱንና የባሳንን ንጉሥ የዐግን ምድር፥ በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩትን የሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ምድር፥ 48በአርኖን ወንዝ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ እስከ ሲዎን ተራራ እስከ አርሞንዔም ድረስ፥ 49በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ከፈስጋ ተራራ በታች ያለውን ዓረባ ሁሉ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ወሰዱ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in