YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ገላትያ ሰዎች 1

1
1-2በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፦
3ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። 5ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።
6በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ 7እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። 8ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። 9አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።
10ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም።
11ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ 12ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። 13በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ 14ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። 15-16ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ 17ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።
18ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ 19ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 20ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። 21ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። 22በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ 23ነገር ግን፦ ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ 24ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in