YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ኢሳይያስ 44

44
1አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ። 2የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር እንዲህ ያልል፦ ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ። 3በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፥ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥ 4በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ። 5ይህ፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፥ ይህም፦ እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል በእስራኤልም የቍልምጫ ስም ይጠራል። 6የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። 7እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፥ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ። 8አትፍሩ አትደንግጡም፥ ከጥንቱም ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፥ ማንንም አላውቅም። 9የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፥ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፥ ስለዚህ ያፍራሉ። 10አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው? 11እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፥ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፥ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ። 12ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሠጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል። 13ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለከዋል፥ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል። 14የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፥ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፥ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል። 15ለሰውም ማገዶ ይሆናል፥ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፥ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፥ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል። 16ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፥ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፥ ይሞቃልና፦ እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ ይላል። 17የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፥ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግድበታል፥ ወደ እርሱም እየጸለየ፦ አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል። 18አያውቁም፥ አያስቡም፥ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉም ልቦቻቸውን ጨፍነዋል። 19በልቡም ማንም አያስብም፦ ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፥ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም። 20አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም፦ በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም። 21ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፥ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም ባሪያዬ ነህ፥ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳህ ትሆናለህ። 22መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፥ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ። 23ሰማያት ሆይ፥ እግዚአብሔር አድርጎታልና ዘምሩ፥ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፥ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ። 24ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ከእኔ ጋር ማን ነበረ? 25የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፥ 26የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፥ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፥ ኢየሩሳሌምን፦ የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች፦ ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ፥ 27ቀላዩም፦ ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፥ 28ቂሮስንም፦ እርሱ እረኛዬ ነው፥ እርሱም ኢየሩሳሌምን፦ ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Video for ትንቢተ ኢሳይያስ 44