መጽሐፈ መሳፍንት 17
17
1በተራራማውም በኤፍሬም አገር ሚካ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። 2እናቱንም፦ ከአንቺ ዘንድ የተወሰደው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር፥ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፥ እኔም ወስጄዋለሁ አላት። እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ አለችው። 3አንዱን ሺህ እንዱን መቶ ብርም መለሰላት፥ እናቱም፦ ይህን ብር የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጌ ከእጄ ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፥ አሁንም ለአንተ እመልሰዋለሁ አለች። 4ለእናቱም ገንዘቡን በመለሰላት ጊዜ እናቱ ሁለቱን መቶ ብር ወስዳ ለአንጥረኛ ሰጠችው፥ እርሱም የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አደረገው። ያም በሚካ ቤት ነበረ። 5ሰውዮውም ሚካ የአምላክ ቤት ነበረው፥ ኤፉድና ተራፊም አደረገ፥ ከልጆቹም አንዱን ቀደሰው፥ ካህንም ሆነለት። 6በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፥ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።
7በቤተ ልሔም ይሁዳም ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ጕልማሳ ነበረ፥ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፥ በዚያም ይቀመጥ ነበር። 8ይህም ሰው የሚቀመጥበትን ስፍራ ለመሻት ከከተማው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ወጣ፥ ሲሔድም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም አገር ወደ ሚካ ቤት መጣ። 9ሚካም፦ ከወዴት መጣህ? አለው። እርሱም፦ ከቤተ ልሔም ይሁዳ የሆንሁ ሌዋዊ ነኝ፥ የምቀመጥበትንም ስፍራ ለመሻት እሄዳለሁ አለው። 10ሚካም፦ ከእኔ ዘንድ ተቀመጥ፥ አባትና ካህንም ሁነኝ፥ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በየዓመቱም አሥር ብር እሰጥሃለሁ አለው። ሌዋዊውም ገባ። 11ሌዋዊውም ከሰውዮው ጋር መቀመጥን ፈቀደ፥ ጕልማሳውም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። 12ሚካም ሌዋዊውን ቀደሰ፥ ጕልማሳውም ካህኑ ሆነለት፥ በሚካም ቤት ነበረ። 13ሚካም፦ ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ አለ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 17: አማ54
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in