YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 7

7
1-2እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። 3በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? 4ወይም ወንድምህን፦ ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። 5አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
6በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።
7ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። 8የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። 9ወይስ ከእናንተ ልጁ እንጀራ ቢለምነው ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? 10ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? 11እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? 12እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።
13በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ 14ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
15የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። 16ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? 17እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። 18መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። 19መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 20ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
21በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። 22በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። 23የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።
24ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። 25ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። 26ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። 27ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።
28ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን፥ 29እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for የማቴዎስ ወንጌል 7