YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 6

6
1ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና፦ እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? 3ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። 4ኢየሱስም፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። 5በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። 6ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ።
በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር።
7አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ 8ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። 9በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። 10በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። 11ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። 12ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ 13ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
14ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ፦ መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። 15ሌሎችም፦ ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም፦ ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ። 16ሄሮድስ ግን ሰምቶ፦ እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ። 17ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ 18ዮሐንስ ሄሮድስን፦ የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና። 19ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤ 20ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤ 21በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና 22የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን፦ የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤ 23የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትለምኚውን ሁሉ እሰጥሻለሁ ብሎ ማለላት። 24ወጥታም ለእናትዋ፦ ምን ልለምነው? አለች። እርስዋም፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ አለች። 25ወዲያውም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ ብላ ለመነችው። 26ንጉሡም እጅግ አዝኖ ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ስለ ተቀመጡት ሊነሣት አልወደደም። 27ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ 28ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። 29ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።
30ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። 31እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። 32በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። 33ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። 34ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። 35በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤ 36የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት። 37እርሱ ግን መልሶ፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት። 38እርሱም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ፦ አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት። 39ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው። 40መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ። 41አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ 42ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ። 44እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ።
45ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 46ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 47በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ። 48ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር። 49እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥ 50ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው። 51ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤ 52ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።
53ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ። 54ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት 55በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር። 56በገባበትም ስፍራ ሁሉ፥ መንደርም ከተማም ገጠርም ቢሆን፥ በገበያ ድውዮችን ያኖሩ ነበር፤ የልብሱንም ጫፍ እንኳ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in