YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘኊልቊ 20

20
1የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች። 2ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ። 3ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት፦ ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ! 4እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ? 5ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም። 6ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። 7እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 8በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ። 9ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ። 10ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው፦ እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው። 11ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ። 12እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን፦ በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው። 13የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ ጠብ ያደረጉበት፥ እርሱም ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው። 14ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ፦ ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ 15አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤ 16ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ሰድዶ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል። 17እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም። 18ኤዶምያስም፦ በሰይፍ እንዳልገጥምህ በምድሬ ላይ አታልፍም አለው። 19የእስራኤልም ልጆች፦ በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ አሉት። 20እርሱም፦ አታልፍም አለ። 21ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ። ኤዶምያስም እስራኤል በዳርቻው እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ። 22ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ። 23እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 24አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በቃሌ ላይ ስለ ዓመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም። 25አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤ 26ከአሮንም ልብሱን አውጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማች፥ በዚያም ይሙት። 27ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ። 28ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ። 29ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in