YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘኊልቊ 27

27
1ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። 2በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው፦ 3አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም። 4ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን አሉ። 5ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ። 6እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 7የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ። 8ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ፤ 9ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ስጡ፤ 10ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ፤ 11የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ስጡ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን። 12እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤ 13ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ። 14እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው። 15ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 16-17የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በፊታቸው የሚወጣውን በፊታቸውም የሚገባውን የሚያስወጣቸውንም የሚያስገባቸውንም ሰው የሥጋ ሁሉ መንፈስ አምላክ እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ ይሹመው። 18እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤ 19በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው። 20የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት። 21በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ። 22ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤ 23እግዚአብሔርም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በላዩ ጫነበት፥ አዘዘውም።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in