YouVersion Logo
Search Icon

ሐዋርያት ሥራ 7

7
እስጢፋኖስ በሸንጎው ፊት ያደረገው ንግግር
1ሊቀ ካህናቱም፣ “ይህ የቀረበብህ ክስ እውነት ነውን?” አለው።
2እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አድምጡኝ! አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፣ 3‘ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ’ አለው።
4“እርሱም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከአባቱም ሞት በኋላ፣ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ አገር አመጣው። 5በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታህል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከእርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት። 6ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ቀንበር ሥር ይማቅቃል። 7ሆኖም በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ። ከዚያም አገር ወጥተው በዚህች ስፍራ ያመልኩኛል።’ 8ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ።
9“የነገድ አባቶችም በዮሴፍ ቀንተው በባርነት ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ 10ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብፅም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብፅና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።
11“በዚያ ጊዜም በግብፅና በከነዓን አገር ሁሉ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን ዐጡ። 12ያዕቆብም እህል በግብፅ መኖሩን በሰማ ጊዜ፣ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ ላካቸው፤ 13ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ደግሞ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ዘመዶች ተረዳ። 14ከዚህ በኋላ፣ ዮሴፍ ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የሚሆኑ ቤተ ዘመዶቹን በሙሉ አስመጣ። 15ያዕቆብ ወደ ግብፅ ወረደ፤ እርሱም አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ። 16አስከሬናቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ፣ አብርሃም ከዔሞር ልጆች ላይ በጥሬ ብር በገዛው መቃብር ተቀበረ።
17“እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብም፣ በግብፅ የነበረው የሕዝባችን ቍጥር እየበዛ ሄደ። 18ከዚያ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ ነገሠ። 19እርሱም ሕዝባችንን በተንኰሉ አስጨነቀ፤ ገና የተወለዱ ሕፃናታቸውም ይሞቱ ዘንድ ወደ ውጭ አውጥተው እንዲጥሏቸው አስገደዳቸው።
20“በዚህ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ውብ ሕፃን#7፥20 ወይም ተራ ልጅ አልነበረም ነበር። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ አደገ። 21ወደ ውጭ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አግኝታ ወሰደችው፤ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋም አሳደገችው። 22ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።
23“ሙሴ አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኝ በልቡ ዐሰበ። 24እርሱም፣ አንድ ግብፃዊ ከወገኖቹ አንዱን በደል ሲያደርስበት አይቶ ግብፃዊውንም ገደለ፤ ለተገፋው ወገኑም ተበቀለ። 25ወገኖቹም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም። 26በማግስቱም ደግሞ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ደረሰ፤ ሊያስታርቃቸውም ፈልጎ፣ ‘ሰዎች፤ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?’ አላቸው።
27“በባልንጀራው ላይ በደል ሲያደርስ የነበረው ሰው ግን፣ ሙሴን ገፈተረውና እንዲህ አለ፤ ‘አንተን ገዥና ፈራጅ አድርጎ በእኛ ላይ የሾመህ ማን ነው? 28ወይስ ትናንት ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋልህን?’ 29ሙሴም ይህን እንደ ሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ተቀመጠ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።
30“ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በሲና ተራራ አካባቢ ባለው ምድረ በዳ፣ በሚነድድ ቍጥቋጦ ነበልባል ውስጥ መልአክ ተገለጠለት። 31ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ፤ ነገሩን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የጌታ ድምፅ፤ 32‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ሲል ሰማ። ሙሴም በፍርሀት ተዋጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም።
33“ጌታም እንዲህ አለው፤ ‘የእግርህን ጫማ አውልቅ፤ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና። 34በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብፅ መልሼ እልክሃለሁ።’
35“እንግዲህ እነዚያ፣ ‘ገዥና ፈራጅ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህን ሙሴ እግዚአብሔር በቍጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው። 36እርሱም መርቶ ከግብፅ አወጣቸው፤ በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ።
37“የእስራኤልንም ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከመካከላችሁ ያስነሣላችኋል’ ያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር። 38እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ።
39“አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ ሊታዘዙት ስላልፈለጉ በልባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ። 40አሮንንም፣ ‘ፊት ፊታችን የሚሄዱ አማልክት አብጅልን፤ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና’ አሉት። 41በዚያን ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም። 42እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤
“ ‘እናንት የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ በነበራችሁ ጊዜ፣
መሥዋዕትንና መባን ለእኔ አቀረባችሁልኝን?
43ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን፣
የሞሎክን ድንኳንና የጣዖታችሁን፣
የሬምፉምን ኮከብ ከፍ ከፍ አድርጋችሁ ያዛችሁ።
ስለዚህ እኔም እንድትጋዙ አደርጋለሁ፤ ከባቢሎንም ወዲያ እሰድዳችኋለሁ።’
44“እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ንድፍና ባዘዘው መሠረት የተሠራችው የምስክር ድንኳን፣ ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ ነበረች። 45አባቶቻችንም ድንኳኗን ከተቀበሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ ይዘዋት ገቡ፤ እስከ ዳዊትም ዘመን ድረስ በምድሪቱ ተቀመጠች፤ 46ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ ለያዕቆብ#7፥46 አንዳንድ የጥንት ቅጆች የያዕቆብ ቤት ይላሉ። አምላክ ማደሪያ ያዘጋጅ ዘንድ ለመነ፤ 47ነገር ግን የማደሪያውን ቤት የሠራለት ሰሎሞን ነበር።
48“ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤
49“ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤
ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤
ታዲያ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ?
ይላል ጌታ፤
ወይንስ ማረፊያ የሚሆነኝ የትኛው ቦታ ነው?
50ይህን ሁሉ የሠራው እጄ አይደለምን?’
51“እናንት ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ፣ ዐንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ። 52ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤ 53በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።”
የእስጢፋኖስ መወገር
54በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ፤ ጥርሳቸውንም አፏጩበት። 55እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣ 56“እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።
57በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሯቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤ 58ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጕልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።
59እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት፤” ብሎ ጸለየ፤ 60ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው!” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in