የሉቃስ ወንጌል 24
24
የኢየሱስ ከሞት መነሣት
(ማቴ. 28፥1-10፤ ማር. 16፥1-8፤ ዮሐ. 20፥1-10)
1ሴቶቹ ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) ጠዋት በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ 2መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት። 3ወደ ውስጥ በገቡ ጊዜ ግን የጌታ ኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። 4ስለዚህም ነገር በመገረም ላይ ሳሉ እነሆ፥ የሚያንጸባርቅ ብሩህ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች መጥተው በአጠገባቸው ቆሙ። 5ሴቶቹም እጅግ ፈርተው ወደ መሬት አቀርቅረው ሳሉ ሰዎቹ፦ “ስለምን ሕያውን ከሙታን መካከል ትፈልጋላችሁ? አሉአቸው። 6እርሱ እዚህ የለም፤ ተነሥቶአል፤ በገሊላ በነበረበት ጊዜ የነገራችሁን አስታውሱ፤ 7‘የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች ተላልፎ መሰጠት፥ መሰቀልና በሦስተኛውም ቀን ከሞት መነሣት ይገባዋል’ ብሎአችሁ ነበር።” #ማቴ. 16፥21፤ 17፥22-23፤ 20፥18-19፤ ማር. 8፥31፤ 9፥31፤ 10፥33-34፤ ሉቃ. 9፥22፤ 18፥31-33።
8ሴቶቹም የኢየሱስን ቃል አስታወሱ፤ 9ከመቃብርም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለቀሩትም ነገሩአቸው። 10ይህን ለሐዋርያት የተናገሩት መግደላዊት ማርያም፥ ዮሐናና የያዕቆብ እናት ማርያም፥ እንዲሁም ሌሎች ሴቶች ነበሩ። 11እነርሱ ግን ይህ ነገር ቅዠት ስለ መሰላቸው አላመኑአቸውም። 12ነገር ግን ጴጥሮስ ተነሥቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ፤ እዚያም ሲደርስ ጐንበስ ብሎ በተመለከተ ጊዜ አስከሬኑ የተከፈነበትን ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀመጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤት ተመለሰ።
ኢየሱስ ለሁለት ደቀ መዛሙርት መገለጡ
(ማር. 16፥12-13)
13በዚያኑ ቀን ከኢየሱስ ተከታዮች ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያኽል ርቃ ወደምትገኝ ኤማሁስ ተብላ ወደምትጠራ መንደር ይጓዙ ነበር። 14እነርሱም ይህን የሆነውን ነገር ሁሉ አንሥተው እርስ በእርሳቸው ይወያዩ ነበር። 15ይህንንም በሚያወሩበትና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሮአቸው ይጓዝ ጀመር። 16ነገር ግን በዐይናቸው እያዩት ማን እንደ ሆነ ማወቅ አልቻሉም። 17እርሱም “በጒዞ ላይ ሳላችሁ የምትነጋገሩበት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው።
እነርሱም እያዘኑ ቀጥ ብለው ቆሙ። 18ከእነርሱም አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው፥ “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” አለው።
19ኢየሱስም “ምንድን ነው እርሱ?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለ ተፈጸመው ነገር ነዋ! እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች ሁሉ ፊት በቃልና በሥራ ብርቱ የሆነ ነቢይ ነበር። 20የካህናት አለቆችና መሪዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ እንዲሁም ሰቀሉት። 21እኛ ግን ‘እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው’ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ እነሆ፥ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። 22እንዲያውም ከእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ ሴቶች አስገርመውናል፤ እነርሱ ዛሬ በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ 23ነገር ግን የእርሱን አስከሬን አላገኙም፤ ‘ሕያው ሆኖአል!’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን እያሉም ተመልሰው መጡ። 24ከእኛም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙ፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።”
25ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉና ነቢያት የተናገሩትንም ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! 26መሲሕ ይህን ሁሉ መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” 27ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት መጻሕፍት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ አስረዳቸው።
28እነርሱ ወደሚሄዱበት መንደር በቀረቡ ጊዜ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። 29እነርሱ ግን “ቀኑ መሽቶአል፤ ፀሐይም መጥለቅዋ ነው፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር እዚህ ዕደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋር ሊያድር ወደ ቤት ገባ። 30ከእነርሱም ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ እንጀራ አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ቈርሶ ሰጣቸው። 31በዚያን ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተና ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ ግን ወዲያው ከዐይናቸው ተሰወረ። 32እነርሱም እርስ በርሳቸው “በመንገድ ሳለን ሲነግረንና ቅዱሳት መጻሕፍትንም እየጠቀሰ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠል አልነበረምን?” ተባባሉ።
33እነርሱም በዚያችው ሰዓት ተነሡና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ፤ በዚያም ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርት አብረዋቸው ካሉት ጋር በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። 34እነርሱም “ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል!” ይሉ ነበር።
35ሁለቱም ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው በመንገድ ላይ የሆነውን ነገርና ጌታ ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁትም ተረኩላቸው።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መገለጡ
(ማቴ. 28፥16-20፤ ማር. 16፥14-18፤ ዮሐ. 20፥19-23፤ ሐ.ሥ. 1፥6-8)
36እነርሱም ይህን ሲናገሩ ሳሉ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው።
37እነርሱ ግን መንፈስ የሚያዩ መስሎአቸው ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ። 38ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትደነግጣላችሁ፤ ስለምንስ በልባችሁ ትጠራጠራላችሁ? 39እጆቼንና እግሮቼን አይታችሁ እኔ ራሴ መሆኔን ዕወቁ፤ ዳሳችሁም እዩኝ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም።”
40ይህንንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው፤ 41እነርሱም ከደስታና ከአድናቆት ብዛት የተነሣ ገና አላመኑም ነበር። ኢየሱስም “አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። 42እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት። 43እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።
44ኢየሱስም፥ “ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ የነገርኳችሁ ቃል ይህ ነው” አላቸው።
45ከዚህ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተዋል እንዲችሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው። 46እንዲህም አላቸው፤ “መሲሕ መከራ እንደሚቀበልና በሦስተኛው ቀን ከሞት እንደሚነሣ አስቀድሞ ተጽፎአል፤ 47እንዲሁም በስሙ የንስሓና የኃጢአት ይቅርታ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በየአገሩ ለሕዝብ ሁሉ እንደሚሰበክ ተነግሮአል። 48እናንተም የዚህ ሁሉ ነገር ምስክሮች ናችሁ፤ 49እነሆ! እኔ አባቴ የሰጣችሁን ተስፋ እልክላችኋለሁ፤ እናንተም ከላይ ኀይል እንደ ልብስ እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ።” #ሐ.ሥ. 1፥4።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደ ዐረገ
(ማር. 16፥19-20፤ ሐ.ሥ. 1፥9-11)
50ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከኢየሩሳሌም ከተማ አውጥቶ እስከ ቢታንያ ወሰዳቸው፤ በዚያም እጆቹን ዘርግቶ ባረካቸው። 51ሲባርካቸውም ሳለ ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ሰማይ ዐረገ። #ሐ.ሥ. 1፥9-11። 52እነርሱም ሰገዱለትና በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 53እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ዘወትር ከቤተ መቅደስ አይለዩም ነበር።
S'ha seleccionat:
የሉቃስ ወንጌል 24: አማ05
Subratllat
Comparteix
Copia
Vols que els teus subratllats es desin a tots els teus dispositius? Registra't o inicia sessió
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997