የዮሐንስ ወንጌል 4

4
ኢየሱስና ሳምራዊቷ ሴት
1እንግዲህ “ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል፤ ያጠምቅማል፤” መባሉን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ 2ምንም እንኳን ደቀመዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ እራሱ ባያጠምቅም፤ 3የይሁዳን ምድር ትቶ ወደ ገሊላ እንደገና ሄደ። 4በሰማርያም ማለፍ ግድ ሆነበት። 5#ዘፍ. 33፥19፤ ኢያ. 24፥32።ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትገኝ ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ 6በዚያም የያዕቆብ ጉድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ።
7አንዲት የሰማርያ ሴት ውሃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ 8ደቀመዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። 9#ዕዝ. 4፥1-5፤ ነህ. 4፥1፤2።ስለዚህ ሳምራዊቲቱ “አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ?” አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። 10ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ወሃ አጠጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ፥ አንቺ በለመንሽው ነበር፤ የሕይወትም ውሃ በሰጠሽ ነበር፤” አላት። 11ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! መቅጃ የለህም፤ ጉድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውሃ ከወዴት ታገኛለህ? 12በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል፤” አለችው። 13ኢየሱስም መልሶ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ 14እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል እንጂ፤” አላት። 15ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! እንዳልጠማ ውሃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውሃ ስጠኝ፤” አለችው።
16ኢየሱስም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ፤” አላት። 17ሴቲቱ መልሳ “ባል የለኝም፤” አለችው። ኢየሱስም “‘ባል የለኝም፤’ በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ 18አምስት ባሎች ነበሩሽና፤ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነቱን ተናገርሽ፤” አላት። 19ሴቲቱ “ጌታ ሆይ! አንተ ነቢይ እንደሆንህ አያለሁ። 20አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ ‘ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው፤’ ትላላችሁ፤” አለችው። 21ኢየሱስም እንዲህ አላት “አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። 22እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ለምናውቀው እንሰግዳለን፥ መዳን ከአይሁድ ነውና። 23ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ ይኸውም አሁን ነው፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ 24እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።” 25ሴቲቱ “ክርስቶስ የሚባል መሢሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል፤” አለችው። 26ኢየሱስ “የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ፤” አላት።
27በዚያም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን “ምን ፈለግህ?” ወይም “ስለምን ትናገራታለህ?” ያለ ማንም አልነበረም። 28ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች፤ ለሰዎቹም 29“ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” አለች። 30ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።
31ይህም ሲሆን ሳለ ደቀመዛሙርቱ “መምህር ሆይ! ብላ፤” ብለው ለመኑት። 32እርሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ፤” አላቸው። 33ስለዚህ ደቀመዛሙርቱ “የሚበላው አንዳች ምግብ ሰው አምጥቶለት ይሆንን?” ተባባሉ። 34ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ ማድረግ፥ ሥራውንም መፈጸም ነው። 35እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶአል፤ ከዚያም መከር ይመጣል፤’ ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፤ ዐይናችሁን አንሡ፤ እርሻው ከወዲሁ ለአዝመራ እንዴት እንደ ደረሰ ተመልከቱ። 36የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል፤ የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘለዓለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል። 37‘አንዱ ይዘራል፤ አንዱም ያጭዳል፤’ የሚለው ቃል በዚህ እውነት ሆኖአልና። 38እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኋችሁ፤ ሌሎች ደከሙ፤ እናንተም እነርሱ በደከሙበት ገባችሁ።”
39ሴቲቱም “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ፤” ብላ በመሰከረችው ቃል መሠረት፥ ከዚያች ከተማ፥ ብዙ የሰማርያ ሰዎች በእርሱ አመኑ። 40የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ለሁለት ቀን ያህል ቆየ። 41በቃሉ ምክንያት ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ፤ 42ሴቲቱንም “አሁን የምናምነው በቃልሽ ምክንያት አይደለም፤ እኛ እራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱ በእውነት የዓለም መድኃኒት እንደሆነ እናውቃለን፤” ይሉአት ነበር።
ኢየሱስ የሹሙን ልጅ አንደ ፈወሰ
(ማቴ. 8፥5-13ሉቃ. 7፥1-10)
43ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ። 44#ማቴ. 13፥57፤ ማር. 6፥4፤ ሉቃ. 4፥24።ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና። 45#ዮሐ. 2፥23።ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች፥ እራሳቸውም ለበዓል መጥተው ነበርና፥ በበዓል በኢየሩሳሌም ያደረገውን ሁሉ ስላዩ ተቀበሉት።
46 # ዮሐ. 2፥1-11። ኢየሱስም ውሃውን የወይን ጠጅ ወዳደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ። በቅፍርናሆምም ልጁ የታመመበት ከንጉሥ ቤት አንድ ሹም ነበረ። 47እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ እንደመጣ ሰምቶ፥ ልጁ ሊሞት ስለ ቀረበ፥ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወርዶም እንዲፈውስለት ለመነው። 48ስለዚህም ኢየሱስ “ምልክትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ ከቶ አታምኑም፤” አለው። 49ሹሙም “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሳይሞት ውረድ፤” አለው። 50ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ፤” አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ። 51እርሱም ሲወርድ ሳለ አገልጋዮቹ ተገናኙትና “ብላቴናህ በሕይወት አለ፤” ብለው ነገሩት። 52እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም “ትናንት በሰባት ሰዓት ትኩሳቱ ለቀቀው፤” አሉት። 53አባቱም፥ ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት አለ፤” ባለው በዚያ ሰዓት እንደሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋር አመነ። 54ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ምልክት ነው።

Subratllat

Comparteix

Copia

None

Vols que els teus subratllats es desin a tots els teus dispositius? Registra't o inicia sessió