የሉቃስ ወንጌል 23
23
ጌታችን በጲላጦስ ፊት ስለ መቆሙ
1ሁሉም በሙሉ ተነሥተው ወደ ጲላጦስ ወሰዱት። 2እንዲህም እያሉ ይከስሱት ጀመር፥ “ይህ ሰው ለቄሣር ግብር እንዳይሰጡ ሲከለክልና ሕዝቡን ሲያሳምፅ፥ ራሱንም የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስን ሲያደርግ አገኘነው።” 3ጲላጦስም፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ እንደ ሆንሁ አንተ አልህ” አለው። 4ጲላጦስም ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ፥ “በዚህ ሰው ላይ ያገኘሁት አንድስ እንኳ በደል የለም” አላቸው። 5ሕዝቡም፥ “ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በመላው ይሁዳ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል” እያሉ አጽንተው ጮኹ።
ጌታችን በሄሮድስ ፊት ስለ መቆሙ
6ጲላጦስም “ገሊላ” ሲሉ ሰምቶ፤ ሰውየዉ ገሊላዊ እንደ ሆነ የገሊላን ሰዎች ጠየቀ። 7ከሄሮድስ ግዛትም ውስጥ መሆኑን ዐውቆ ወደ ሄሮድስ ላከው፤ ሄሮድስ በዚያ ወራት በኢየሩሳሌም ነበርና። 8ሄሮድስም ጌታችን ኢየሱስን ባየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው፤ ዜናውን ስለሚሰማ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሊያየው ይሻ ነበርና፤ የሚያደርገውንም ተአምራት ሊያይ ይመኝ ነበርና። 9በብዙ ነገርም መረመረው፤ እርሱ ግን አንድስ እንኳ አልመለሰለትም። 10የካህናት አለቆችና ጻፎችም ቆመው በብዙ ያሳጡት ነበር። 11ሄሮድስም ከሠራዊቱ ጋር አቃለለው፤ አፌዘበትም፤ የሚያንፀባርቅ ልብስም አልብሶ ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። 12በዚያም ቀን ሄሮድስና ጲላጦስ ተስማሙ፤ ቀድሞ ጥል ነበራቸውና።
13ጲላጦስም የካህናት አለቆችንና መኳንንቱን፥ ሕዝቡንም ጠራቸው። 14እንዲህም አላቸው፥ “ይህን ሰው ሕዝብን ያሳምፃል ብላችሁ ወደ እኔ አመጣችሁት፤ በፊታችሁም እነሆ፥ መረመርሁት፤ ግን እናንተ ካቀረባችሁት ክስ በዚህ ሰው ላይ ያገኘሁት አንዳች በደል የለም። 15ወደ ሄሮድስም ሰድጃችሁ ነበር፤ እርሱም ምንም ስላላገኘበት ወደ እኛ መልሶታል፤ ለሞትም የሚያበቃ ያደረገው ነገር የለም። 16እነሆ፥ እኔም እንግዲህ ገርፌ ልተወው” አለ።
በርባን ስለ መፈታቱና በጌታ ስለ መፈረዱ
17በየበዓሉም ከእስረኞች አንድ ሊፈታላቸው ልማድ ነበር። 18ሁሉም በሙሉ፥ “ይህን አስወግደው፥ ስቀለውም፥#“ስቀለው” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። በርባንን ግን ፍታልን” ብለው ጮሁ። 19ያ በርባን ግን በከተማ ሁከት ያደረገና ነፍስ በመግደል የታሰረ ነበር። 20ጲላጦስም ኢየሱስን ሊፈታው ወድዶ፥ “ ኢየሱስን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?” ብሎ እንደ ገና ተናገራቸው። 21እነርሱ ግን፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ይጮሁ ነበር። 22ጲላጦስም ለሦስተኛ ጊዜ፥ “ምን ክፉ ነገር አደረገ? እነሆ፥ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት አላገኘሁበትም፤ እንኪያስ ልግረፈውና ልተወው” አላቸው። 23እንዲሰቅሉትም ቃላቸውን ከፍ አድርገው እየጮሁ ለመኑ፤ ጩኸታቸውና የካህናት አለቆች ድምፅም በረታ። 24ጲላጦስም የለመኑት ይሆንላቸው ዘንድ ፈረደበት። 25ያን የለመኑትን፥ ነፍስ በመግደልና ሁከት በማድረግ የታሰረውንም ሰው ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
ወደ መስቀል ጕዞ
26በወሰዱትም ጊዜ የቀሬና ሰው ስምዖንን ከዱር ሲመለስ ያዙት፤ ከጌታችን ከኢየሱስም በስተኋላ መስቀሉን አሸከሙት። 27ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሴቶችም “ዋይ ዋይ” እያሉ ያዝኑለትና ያለቅሱለት ነበሩ። 28ጌታችን ኢየሱስም መለስ ብሎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ሆይ፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ እንጂ ለእኔስ አታልቅሱልኝ። 29መካኖች፥ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው የሚሉበት ወራት ይመጣልና። 30#ሆሴዕ 10፥8፤ ራእ. 6፥16። ያንጊዜም ተራሮችን ‘በላያችን ውደቁ፤ ኮረብቶችንም ሰውሩን’ ይሉአቸዋል። 31በዚህ ርጥብ ዕንጨት እንዲህ ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?”
ከወንበዴዎች ጋር ስለ መሰቀሉ
32ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችንም ከእርሱ ጋር ሊሰቅሉ ወሰዱ። 33ቀራንዮ ወደሚባለው ቦታ በደረሱ ጊዜም፥ በዚያ ሰቀሉት፤ እነዚያንም ሁለት ወንበዴዎች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። 34#መዝ. 21፥18። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን ኣያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ፤ በልብሱም ላይ ዕጣ ተጣጣሉና ተካፈሉ። 35#መዝ. 21፥7። ሕዝቡም ቆመው ይመለከቱ ነበር፤ አለቆችም፥ “ሌሎችን አዳነ፤ በእግዚአብሔር የተመረጠ ክርስቶስ ከሆነ ራሱን ያድን” እያሉ ያፌዙበት ነበር። 36#መዝ. 68፥21። ጭፍሮችም ይዘብቱበት ነበር፤ ወደ እርሱም ቀርበው ሆምጣጤ አመጡለት። 37እንዲህም ይሉት ነበር፥ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህስ ራስህን አድን።” 38በራስጌውም ደብዳቤ ጻፉ፤ ጽሕፈቱም በሮማይስጥ፥ በጽርዕና በዕብራይስጥ ሆኖ “የአይሁድ ንጉሣቸው ይህ ነው” የሚል ነበር።
ስለ ሁለቱ ወንበዴዎች
39አብረው ተሰቅለው ከነበሩት አንዱ ወንበዴ፥ “አንተስ ክርስቶስ ከሆንህ ራስህን አድን፤ እኛንም አድነን” ብሎ ተሳደበ። 40ጓደኛውም መልሶ ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፥ “አንተ በዚህ ፍርድ ውስጥ ሳለህ እግዚአብሔር አምላክህን#“አምላክህን” የሚለው በግሪኩ የለም። አትፈራውምን? 41በእኛስ በሚገባ ተፈርዶብናል፤ እንደ ሥራችንም ፍዳችንን ተቀበልን፤ ይህ ግን ምንም የሠራው ክፉ ሥራ የለም።” 42ጌታችን ኢየሱስንም፥ “አቤቱ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ ዐስበኝ” አለው። 43ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ።”
ጌታ ስለ መሞቱና ስለ ተአምራቱ
44ቀትር በሆነ ጊዜም በስድስት ሰዓት ፀሐይ ጨለመ፤ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስም ዓለም ሁሉ #በግሪኩ “ምድር ሁሉ” ይላል። ጨለማ ሆነ። 45#ዘፀ. 26፥31-33። ፀሐዩም በጨለመ ጊዜ የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች#“ከላይ እስከ ታች” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። ከመካከሉ ተቀደደ። 46#መዝ. 30፥5። ያንጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በአንተ እጅ አደራ እሰጣለሁ” ብሎ ጮኸ፤ ይህንም ብሎ ነፍሱን ሰጠ። 47የመቶ አለቃውም የሆነውን ነገር አይቶ፥ “ይህ ሰው በእውነት ጻድቅ ነበረ”ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነው። 48ይህንም ለማየት ተሰብስበው የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የሆነውን ባዩ ጊዜ፥ ደረታቸውን እየመቱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። 49#ሉቃ. 8፥2-3። የሚያውቁት ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉትም ሴቶች በሩቁ ቆመው ይህን ያዩ ነበር።
ጌታ ስለ መቀበሩ
50እነሆ፥ በጎና ጻድቅ ሰው፥ የሸንጎ አማካሪም የሆነ ዮሴፍ የሚባል ሰው መጣ። 51እርሱም በአይሁድ በምክራቸውና በሥራቸው አልተባበረም ነበር፤ ሀገሩም የይሁዳ ዕጣ የሚሆን አርማትያስ ነበር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት ተስፋ ያደርግ ነበር። 52ወደ ጲላጦስም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ለመነ። 53ሥጋውንም አውርዶ በበፍታ ገነዘው፤ ማንም ባልተቀበረበት፥ ከድንጋይም በተፈለፈለ መቃብር ቀበረው፤ ታላቅ ድንጋይም አንከባልሎ መቃብሩን ገጥሞ ሄደ።#“ታላቅ ድንጋይም አንከባልሎ መቃብሩን ገጥሞ ሄደ” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። 54ያም ቀን የሰንበት መግቢያ ዐርብ ነበር። 55ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡ ሁለት#በግሪኩ “ሁለት” አይልም። ሴቶች ተከትለው፥ መቃብሩን፥ ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ። ተመልሰውም ሽቱና ዘይት አዘጋጁ፤ ነገር ግን በሰንበት አልሄዱም፤ ሕጋቸው እንዲህ ነበርና።
वर्तमान में चयनित:
የሉቃስ ወንጌል 23: አማ2000
हाइलाइट
शेयर
कॉपी
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in