23
1ጳውሎስም ወደ ሸንጎው ትኵር ብሎ በመመልከት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት በንጹሕ ሕሊና ተመላልሻለሁ” አለ። 2በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ በጳውሎስ አጠገብ የቆሙትን ሰዎች አፉን እንዲመቱት አዘዘ። 3ጳውሎስም፣ “አንተ በኖራ የተለሰንህ ግድግዳ! እግዚአብሔር ደግሞ አንተን ይመታሃል፤ በሕጉ መሠረት ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ፣ ያለ ሕግ ስላስመታኸኝ አንተ ራስህ ሕጉን ጥሰሃል” አለው።
4ጳውሎስ አጠገብ ቆመው የነበሩትም፣ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ደፍረህ ትሰድባለህን?” አሉት።
5ጳውሎስም፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባለማወቄ ነው፤ ‘በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር’ ተብሎ ተጽፏልና” አላቸው።
6ጳውሎስም ሕዝቡ፣ ከፊሎቹ ሰዱቃውያን፣ ከፊሎቹ ፈሪሳውያን መሆናቸውን ስላወቀ፣ “ወንድሞቼ ሆይ፤ እኔ ከፈሪሳዊ የተወለድሁ ፈሪሳዊ ነኝ፣ ለፍርድ የቀረብሁትም የሙታንን ትንሣኤ ተስፋ በማድረጌ ነው” ሲል በሸንጎው ፊት ጮኸ። 7ይህንም በተናገረ ጊዜ፣ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጠብ ተነሣ፤ ሸንጎውም ለሁለት ተከፈለ። 8ሰዱቃውያን የሙታን ትንሣኤ የለም፤ መላእክትም መናፍስትም የሉም የሚሉ ሲሆኑ፣ ፈሪሳውያን ግን በእነዚህ ሁሉ መኖር የሚያምኑ ነበሩ።
9ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ የኦሪት ሕግ መምህራንም ተነሥተው፣ “በዚህ ሰው ላይ ምንም ጥፋት አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይም መልአክ ተናግሮትስ እንደ ሆነ ምን ይታወቃል?” በማለት አጥብቀው ተከራከሩ። 10ጠቡ ከማየሉ የተነሣም አዛዡ ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈራ፤ ስለዚህ ወታደሮቹ ወርደው ከመካከላቸው ነጥቀው ወደ ጦሩ ሰፈር እንዲያስገቡት አዘዘ።
11በሚቀጥለውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አይዞህ! በኢየሩሳሌም እንደ መሰከርህልኝ፣ በሮምም ደግሞ ልትመሰክርልኝ ይገባሃል” አለው።
ጳውሎስን ለመግደል የተደረገ ሤራ
12በነጋም ጊዜ፣ አይሁድ ተሰብስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። በዚህ ሤራ 13የተማማሉትም ከአርባ በላይ ነበሩ። 14እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ አድርገናል። 15እንግዲህ እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ፣ ስለ ጕዳዩ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ከእርሱ እንደምትፈልጉ አስመስላችሁ ጳውሎስን ወደ እናንተ እንዲሰድደው የጦር አዛዡን ለምኑት፤ እኛም ገና ወደዚህ ሳይደርስ ልንገድለው ዝግጁ ነን።”
16ነገር ግን የጳውሎስ የእኅት ልጅ ስለ ሤራው በመስማቱ፣ ወደ ጦሩ ሰፈር ገብቶ ሁኔታውን ለጳውሎስ ነገረው።
17ጳውሎስም ከመቶ አለቆቹ አንዱን ጠርቶ፣ “ይህ ልጅ ለጦር አዛዡ የሚነግረው ነገር ስላለ ወደ እርሱ ውሰደው” አለው። 18እርሱም ወደ ጦር አዛዡ ወሰደው።
የመቶ አለቃውም፣ “እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶኝ፣ ይህ ጕልማሳ የሚነግርህ ነገር ስላለው ወደ አንተ እንዳቀርበው ለመነኝ” አለው።
19አዛዡም የጕልማሳውን እጅ ይዞ ለብቻው ገለል በማድረግ፣ “ልትነግረኝ የምትፈልገው ምንድን ነው?” አለው።
20ልጁም እንዲህ አለው፤ “አይሁድ ስለ እርሱ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የፈለጉ በመምሰል፣ ጳውሎስን ነገ ሸንጎው ፊት እንድታቀርብላቸው ሊለምኑህ ተስማምተዋል። 21ስለዚህ እሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑት ሊገድሉት አድፍጠው እየጠበቁት ነው፤ ደግሞም እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን መልስ እየተጠባበቁ ነው።”
22የጦር አዛዡም፣ “ይህን ለእኔ የገለጥህልኝን ነገር ለማንም እንዳትናገር” ብሎ ጕልማሳውን አስጠንቅቆ አሰናበተው።
ጳውሎስ ወደ ቂሳርያ ተላከ
23ከዚያም ከመቶ አለቆቹ#23፥23 በግሪኩ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም። ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ከምሽቱ ሦስት ሰዓት፣ ወደ ቂሳርያ የሚሄዱ ሁለት መቶ ወታደሮች፣ ሰባ ፈረሰኞችና ሁለት መቶ ባለ ጦር ጭፍራ አዘጋጁ፤ 24ደግሞም ጳውሎስ ተቀምጦበት ወደ አገረ ገዥው ወደ ፊልክስ በደኅና የሚደርስበት ከብት ይዘጋጅ።”
25ደብዳቤም ጻፈ፤ እንዲህ የሚል፦
26ከቀላውዴዎስ ሉስዩስ፤
ለክቡር አገረ ገዥ ለፊልክስ፤
ሰላም ለአንተ ይሁን።
27አይሁድ ይህን ሰው ይዘው ሊገድሉት ነበር፤ ነገር ግን የሮም ዜጋ መሆኑን ስላወቅሁ፣ ከወታደሮቼ ጋር ደርሼ አተረፍሁት። 28ለምን ሊከስሱት እንደ ፈለጉ ለማወቅም ወደ ሸንጓቸው አቀረብሁት። 29የተከሰሰውም ሕጋቸውን በተመለከተ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ። 30አይሁድ ግን በዚህ ሰው ላይ ማሤራቸውን በተረዳሁ ጊዜ፣ ወዲያው ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም ከእርሱ ጋር ያላቸውን ክርክር ለአንተ እንዲያቀርቡ አዘዝኋቸው።
31ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት፣ ጳውሎስን ይዘው በሌሊት እስከ አንቲጳጥሪስ ድረስ ወሰዱት። 32በማግስቱም፣ ፈረሰኞቹ ብቻ እንዲያደርሱት አድርገው፣ ሌሎቹ ወደ ጦር ሰፈር ተመለሱ። 33ፈረሰኞቹም ቂሳርያ በደረሱ ጊዜ፣ ደብዳቤውን ለአገረ ገዡው ሰጡት፤ ጳውሎስንም አስረከቡት። 34አገረ ገዥውም ደብዳቤውን ካነበበ በኋላ፣ ጳውሎስን ከየትኛው አውራጃ እንደ መጣ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ 35“የአንተን ጕዳይ ከሳሾችህ ሲቀርቡ አያለሁ” አለው። ከዚያም ጳውሎስ በሄሮድስ ግቢ ውስጥ እንዲጠበቅ አዘዘ።