Logo YouVersion
Icona Cerca

ሐዋርያት ሥራ 26

26
1አግሪጳም ጳውሎስን፣ “ስለ ራስህ እንድትናገር ተፈቅዶልሃል” አለው።
በዚህ ጊዜ ጳውሎስ እጁን ዘርግቶ እንዲህ ሲል መከላከያውን አቀረበ፤ 2“ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ አይሁድ በእኔ ላይ ላቀረቡት ክስ ሁሉ ዛሬ በፊትህ የመከላከያ መልስ ለማቅረብ በመቻሌ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቈጥረዋለሁ፤ 3ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ።
4“ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በአገሬም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደ ኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤ 5ደግሞም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለሚያውቁኝ ከሃይማኖታችን እጅግ ጥብቅ በሆነው ወገን ውስጥ ሆኜ እንደ አንድ ፈሪሳዊ መኖሬን ሊመሰክሩ ፈቃደኞች ከሆኑ ቃላቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። 6አሁንም ተከስሼ እዚህ የቀረብሁበት ምክንያት፣ እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ቃል የገባውን ነገር ተስፋ በማድረጌ ነው። 7ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ከልብ እያገለገሉ፣ ሲፈጸም ለማየት የሚተጉለትም ተስፋ ይኸው ነው። ንጉሥ ሆይ፤ አይሁድም የሚከስሱኝ ስለዚሁ ተስፋ ነው። 8ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሣት እንደማይችል አድርጋችሁ የምትቈጥሩት ለምንድን ነው?
9“እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም በምችለው መንገድ ሁሉ መቃወም እንዳለብኝ ወስኜ ነበር። 10በኢየሩሳሌምም ያደረግሁት ይህንኑ ነበር፤ ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብዬ ብዙ ቅዱሳንን አሳስሬአለሁ፤ በመገደላቸውም ተስማምቻለሁ፤ 11ላስቀጣቸውም ብዙ ጊዜ ከምኵራብ ምኵራብ እየተዘዋወርሁ፣ የስድብ ቃል እንዲናገሩ አስገድዳቸው ነበር፤ በቍጣም ተሞልቼ በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትዬ አሳደድኋቸው።
12“በዚህ መሠረት አንድ ቀን ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ በምጓዝበት ጊዜ፣ 13ንጉሥ ሆይ፤ እኩለ ቀን ላይ በመንገድ ሳለሁ፣ ብሩህነቱ ከፀሓይ የሚበልጥ ብርሃን በእኔና በባልንጀሮቼ ዙሪያ ከሰማይ ሲያበራ አየሁ፤ 14ሁላችንም በምድር ላይ ወደቅን፤ እኔም በዕብራይስጥ#26፥14 ወይም አራማይክ ቋንቋ፣ ‘ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ? መውጊያውን ብትጋፋ ጕዳቱ በአንተ ይብሳል’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።
15“እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?’ ” አልሁ።
“ጌታም እንዲህ አለኝ፤ ‘እኔ፣ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። 16አሁንም፣ ተነሣና በእግርህ ቁም፤ ስለ እኔ ስላየኸውና ወደ ፊትም ስለማሳይህ ነገር አገልጋይና ምስክር እንድትሆን ልሾምህ ተገልጬልሃለሁ። 17ከገዛ ሕዝብህና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ፤ 18አንተም ዐይናቸውን ትከፍታለህ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸዋለህ፤ እነርሱም የኀጢአትን ይቅርታ ይቀበላሉ፤ በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስት ያገኛሉ።’
19“እንግዲህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ከሰማይ ለታየኝ ራእይ አልታዘዝ አላልሁም፤ 20ነገር ግን በመጀመሪያ በደማስቆ ለሚኖሩ፣ ቀጥሎም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላሉት ሁሉ፣ ከዚያም ለአሕዛብ፣ ንስሓ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ የንስሓም ፍሬ እንዲያሳዩ ገልጬ ተናገርሁ። 21አይሁድም በመቅደስ ይዘው ሊገድሉኝ የሞከሩት በዚሁ ምክንያት ነው። 22የእግዚአብሔር ርዳታ እስከ ዛሬ ስላልተለየኝ፣ እነሆ፤ እዚህ ቆሜ ለትንሹም ለትልቁም እመሰክራለሁ፤ ነቢያትና ሙሴ ይሆናል፣ ይፈጸማል ካሉት በስተቀር አንዳች ነገር አልተናገርሁም፤ 23ይኸውም ክርስቶስ#26፥23 ወይም መሲሕ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።”
24ፊስጦስም የጳውሎስን ንግግር እዚህ ላይ በማቋረጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ጳውሎስ ሆይ፤ አእምሮህን ስተሃል፤ የትምህርትህም ብዛት አሳብዶሃል” አለው።
25ጳውሎስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፤ የምናገረው እውነተኛና ትክክለኛ ነገር እንጂ እብድስ አይደለሁም። 26ይህን የምናገረውን ነገር ንጉሡ ያውቀዋልና፤ በፊቱ በልበ ሙሉነት እናገራለሁ፤ ደግሞም በድብቅ የተደረገ ነገር ባለመኖሩ፣ ከዚህ ነገር አንድም እንደማይሰወርበት ርግጠኛ ነኝ። 27ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፤ ነቢያትን ታምን የለም ወይ? አዎን፤ እንደምታምን ዐውቃለሁ።”
28አግሪጳም ጳውሎስን፣ “እንዲህ በቀላሉ ክርስቲያን የምታደርገኝ ይመስልሃልን?” አለው።
29ጳውሎስም፣ “በቀላሉም ሆነ በብዙ፣ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ፣ ከዚህ ከታሰርሁበት ሰንሰለት በስተቀር፣ እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” አለ።
30ከዚህ በኋላ ንጉሡም፣ አገረ ገዥውም፣ በርኒቄም፣ ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትም ተነሡ፤ 31ወጥተውም ሲሄዱ፣ “ይህ ሰው እንኳን ለሞት፣ ለእስራት የሚያበቃው ነገር አላደረገም” ተባባሉ።
32አግሪጳም ፊስጦስን፣ “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ መልቀቅ ይቻል ነበር” አለው።

Attualmente Selezionati:

ሐዋርያት ሥራ 26: NASV

Evidenziazioni

Condividi

Copia

None

Vuoi avere le tue evidenziazioni salvate su tutti i tuoi dispositivi?Iscriviti o accedi