3
የእግዚአብሔር ታማኝነት
1ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምንድን ነው? መገረዝስ ምን ፋይዳ አለው? 2በየትኛውም መንገድ ጥቅሙ ብዙ ነው፤ ከሁሉ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃል በዐደራ የተሰጠው ለእነርሱ ነው።
3አንዳንዶች እምነት ባይኖራቸውስ? የእነርሱ አለማመን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዋጋ ያሳጣዋልን? 4ፈጽሞ አይሆንም! ሰው ሁሉ ሐሰተኛ፣ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤
“ከቃልህ የተነሣ እውነተኛ፣
በፍርድም ፊት ረቺ ትሆናለህ።”
5የእኛ ዐመፃ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አጕልቶ የሚያሳይ ከሆነ፣ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ሰው ለመከራከር ያህል እግዚአብሔር በእኛ ላይ ቍጣውን ማምጣቱ ትክክል አይደለም ሊባል ነውን? እንደ ሰው ሲታሰብ ማለቴ ነው። 6በርግጥ እንዲህ ሊሆን አይችልም፤ እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ሊፈርድ ይችላል? 7“የእኔ ውሸተኛ መሆን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት የሚያጐላ፣ ክብሩንም የሚጨምርለት ከሆነ፣ ኀጢአተኛ ተብዬ እስካሁን እንዴት ይፈረድብኛል?” በማለት ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል። 8ይህማ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ” ይላሉ በማለት አንዳንዶች እንደሚያስወሩብን ነው፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ ትክክለኛ ነው።
ማንም ጻድቅ አይደለም
9እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን?#3፥9 ወይም እንብሳለንን ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከስሰናቸዋል።
10እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
“ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድም እንኳ፤
11አስተዋይ የለም፤
እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም።
12ሁሉም ተሳስተዋል፤
በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤
በጎ የሚያደርግ ማንም የለም፤
አንድም እንኳ።”
13“ጕረሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤
አንደበታቸው ሽንገላን ያዘወትራል።”
“በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።”
14“አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።”
15“እግራቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣን ነው፤
16በመንገዳቸው ጥፋትና ጕስቍልና ይገኛል፤
17የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”
18“በዐይናቸው ፊት የእግዚአብሔር ፍርሀት የለም።”
19እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደ ሆነ፣ እናውቃለን፤ 20ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም በእርሱ ፊት ጻድቅ ነው ሊባል አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን።
በእምነት የሚገኝ ጽድቅ
21አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። 22ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ 23ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤ 24በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ 25በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤#3፥25 ወይም እግዚአብሔር ቍጣውን በመተው ኀጢአትን ለማስወገድ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ 26በአሁኑ ዘመን ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው።
27ታዲያ ትምክሕት ወዴት ነው? እርሱማ ቀርቷል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። 28ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ እናረጋግጣለን። 29እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን፤ የአሕዛብም አምላክ ነው፤ 30የተገረዘውን በእምነት፣ ያልተገረዘውንም በዚያው እምነት የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። 31ታዲያ እንዲህ ከሆነ ከእምነት የተነሣ ሕግን ዋጋ የሌለው እናደርግ ይሆን? ፈጽሞ አይደረግም፤ ሕጉን እናጸናለን እንጂ።