የዮሐንስ ወንጌል 11
11
ስለ አልዓዛር
1የማርያምና የእኅቷ የማርታ መንደር በሚሆን በቢታንያ ስሙ አልዓዛር የሚባል የታመመ አንድ ሰው ነበር። 2ማርያም ግን ጌታችንን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጕርዋ ያሸችው ናት፤ ወንድምዋ አልዓዛርም ታሞ ነበር። 3እኅቶቹም፥ “ጌታችን ሆይ፥ እነሆ፥ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ላኩ። 4ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አለ፥ “ይህ ደዌ በእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም።”
5ጌታችን ኢየሱስም ማርታንና እኅቷን ማርያምን፥ አልዓዛርንም ይወዳቸው ነበር። 6እንደ ታመመ በሰማ ጊዜM በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ። 7ከዚህም በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ኑ፥ ወደ ይሁዳ ሀገር ደግሞ እንሂድ” አላቸው። 8ደቀ መዛሙርቱም፥ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ሊወግሩህ ይሹ አልነበረምን? ዛሬ ደግሞ አንተ ወደዚያ ልትሄድ ትሻለህን?” አሉት። 9ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚሄድ አይሰናከልም፤ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና። 10በሌሊት የሚሄድ ግን ይሰነካከላል፤ በውስጡ የሚያየው ብርሃን የለምና።” 11ይህንም ለደቀ መዛሙርቱ#“ለደቀ መዛሙርቱ” የሚለው በግሪኩ የለም። ነገራቸው፤ ከዚህም በኋላ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ” አላቸው። 12ደቀ መዛሙርቱም፥ “አቤቱ፥ ከተኛስ ይነቃል፤#“ይነቃል” የሚለው በግሪኩ የለም። ይድናልም” አሉት። 13ጌታችን ኢየሱስም ስለ ሞቱ ተናገረ፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት መስሎአቸው ነበር። 14ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ገልጦ እንዲህ አላቸው፥ “አልዓዛር ሞተ። 15ታምኑም ዘንድ እኔ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ።” 16ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስም፥ ባልንጀሮቹን ደቀ መዛሙርት፥ “እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ” አላቸው።
ጌታችን አልዓዛርን ስለ ማስነሣቱ
17ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቢታንያ ሄደ፤#“ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቢታንያ ሄደ” የሚለው በግሪኩ የለም። ከዚያም በደረሰ ጊዜ ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። 18ቢታንያም ለኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ቅርብ ነበረች። 19ከአይሁድም ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርያምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙዎች ነበሩ። 20ማርታም ጌታችን ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። 21ማርታም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። 22አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ።” 23ጌታችን ኢየሱስም፥ “ወንድምሽስ ይነሣል” አላት። 24ማርታም፥ “ሙታን በሚነሡባት በኋለኛዪቱ ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ” አለችው።
ክርስቶስ ትንሣኤና ሕይወት ስለ መሆኑ
25ጌታችን ኢየሱስም አላት፥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል። 26ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህንስ ታምኛለሽን?” 27እርስዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው።
ጌታችን ለአልዓዛር ስለ ማልቀሱ
28ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅቷን ማርያምንም ቀስ ብላ ጠራችና፥ “እነሆ፥ መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል” አለቻት። 29እርስዋም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፤ ወደ እርሱም ሄደች። 30ጌታችን ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። 31ሊያጽናኑአት መጥተው በቤት ከእርስዋ ጋር የነበሩ አይሁድም ፈጥና ተነሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወንድምዋ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሎአቸው ተከተሉአት። 32ማርያምም ጌታችን ኢየሱስ ወደ አለበት ስፍራ ደረሰችና በአየችው ጊዜ ከእግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። 33ጌታችን ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ፥ ከእርስዋ ጋር የመጡ አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከ። 34እርሱም፥ “የት ቀበራችሁት?” አለ፤ እነርሱም፥ “አቤቱ፥ መጥተህ እይ” አሉት። 35ጌታችን ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። 36አይሁድም፥ “ምን ያህል ይወደው እንደ ነበር እዩ” አሉ። 37ከእነርሱም መካከል፥ “ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይን ያበራው ይህ ሰው ይህስ እንዳይሞት ሊያደርግ ባልቻለም ነበርን?” ያሉ ነበሩ።
38ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ ወደ መቃብሩም ሄደ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበር፤ በላዩም ታላቅ ድንጋይ ተገጥሞበት ነበር። 39ጌታችን ኢየሱስም፥ “ድንጋዩን አንሡ” አላቸው፤ የሟቹ እኅት ማርታም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ ይሆናል” አለችው። 40ጌታችን ኢየሱስም፥ “ብታምናስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልሁሽም ነበርን?” አላት። 41ድንጋዩንም አነሡ፤ ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ፥ ሰምተኸኛልና አመሰግንሃለሁ። 42እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ስላሉት ሰዎች ይህን እናገራለሁ።” 43ይህንም ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸና፥ “አልዓዛር፥ ና፤ ወደ ውጭ ውጣ” አለ። 44ሞቶ የነበረውም እንደ ተገነዘ፥ እጁንና እግሩንም እንደ ታሰረ፥ ፊቱም በሰበን እንደ ተጠቀለለ ወጣ፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንግዲህስ ፍቱትና ተዉት ይሂድ” አላቸው።
45ስለዚህ ከአይሁድም ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን አይተው በእርሱ አመኑ። 46ከእነርሱም መካከል ወደ ፈሪሳውያን ሄደው የከሰሱት#“የከሰሱት” የሚለው በግሪኩ የለም። ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውንም ሁሉ ነገሩአቸው።
ስለ አይሁድ ምክር
47የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፥ “እነሆ፥ ይህ ሰው ብዙ ተአምራት ያደርጋል፤ ምን እናድርግ? 48እንዲሁ ብንተወውም ሁሉ ያምኑበታል፤ የሮም ሰዎችም መጥተው ሀገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል።” 49በዚያችም ዓመት የካህናት አለቃ የነበረው ስሙ ቀያፋ የተባለው ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተስ ምንም አታውቁም። 50ምንም አትመክሩም፤ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻለናል።” 51ይህንም ከልቡ የተናገረው አይደለም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት የካህናት አለቃ ነበርና ጌታችን ኢየሱስ ስለ ሕዝብ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ይሞት ዘንድ ስላለው ይህን ትንቢት ተናገረ። 52ስለ ሕዝብ ብቻ አልነበረም፤ የተበተኑትን የእግዚአብሔርንም ልጆች በአንድነት ይሰበስባቸው ዘንድ ነው እንጂ። 53ከዚያችም ቀን ጀምሮ የካህናት አለቆች ሊገድሉት ተማከሩ።
ጌታችን ኢየሩሳሌምን ትቶ ስለ መሄዱ
54ከዚያም ወዲያ ጌታችን ኢየሱስ በአይሁድ መካከል በግልጥ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን ለምድረ በዳ አቅራቢያ ወደ ሆነች ምድር፥ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።
55የአይሁድም የፋሲካ በዓል ቀርቦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ከበዓሉ አስቀድሞ ራሳቸውን ያነጹ ዘንድ ከየሀገሩ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተው ነበር። 56አይሁድም ጌታችን ኢየሱስን ይፈልጉት ጀመር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው እርስ በርሳቸው፥ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓል አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ። 57የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ያለበትን የሚያውቅ ቢኖር ይይዙት ዘንድ እንዲያመለክታቸው አዘዙ።