ዮሐንስ 3
3
ኢየሱስ ኒቆዲሞስን አስተማረ
1ከፈሪሳውያን ወገን፣ ከአይሁድ አለቆች አንዱ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው ነበረ፤ 2በሌሊትም ወደ ኢየሱስ መጥቶ፣ “ረቢ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ ሰው በቀር አንተ የምታደርጋቸውን ታምራዊ ምልክቶች ማንም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደ ሆንህ እናውቃለን” አለው።
3ኢየሱስም መልሶ፣ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ዳግመኛ ካልተወለደ#3፥3 ወይም ከላይ ካልተወለደ፤ 7 ይመ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው።
4ኒቆዲሞስም፣ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ እንዲወለድ ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀንስ ሊገባ ይችላልን?” አለው።
5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እውነት እልሃለሁ፤ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፤ 6ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደም መንፈስ ነው። 7‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልሁህ አትገረም፤ 8ነፋስ ወደሚወድደው ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደ መጣ፣ ወዴት እንደሚሄድም አታውቅም፤ ከመንፈስም የተወለደ ሁሉ እንደዚሁ ነው።”
9ኒቆዲሞስም፣ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው።
10ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ሳለ እነዚህን ነገሮች አታውቅምን? 11እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉም። 12ስለ ምድራዊው ነገር ነግሬአችሁ ያላመናችሁ፣ ስለ ሰማያዊው ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም።#3፥13 ወይም በሰማይ ካለው… 14ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ 15ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።
16“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዷልና። 17እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው። 18በእርሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም#3፥18 ወይም በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስላላመነ፣ አሁኑኑ ተፈርዶበታል። 19ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ፤ 20ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21በእውነት የሚመላለስ ግን ሥራው በእግዚአብሔር የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታይ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”#3፥21 አንዳንድ ተርጓሚዎች ትምህርተ ጥቅሱን ከቍጥር 15 በኋላ ያደርጋሉ።
መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መሰከረ
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ አገር ሄዱ፤ እዚያም ከእነርሱ ጋር ጥቂት ተቀመጠ፤ አጠመቀም።
23በዚህ ጊዜ ዮሐንስም በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ብዙ ውሃ ስለ ነበረ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም ለመጠመቅ ይመጡ ነበር። 24ይህም የሆነው ዮሐንስ ከመታሰሩ በፊት ነበር። 25በአንዳንድ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአንድ አይሁዳዊ#3፥25 አንዳንድ ቅጆች አንዳንድ አይሁድ ይላሉ። መካከል ስለ መንጻት ሥርዐት ክርክር ተነሣ፤ 26ወደ ዮሐንስም መጥተው፣ “ረቢ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፣ ስለ እርሱም የመሰከርህለት ሰው እነሆ፤ ያጠምቃል። ሰውም ሁሉ ወደ እርሱ እየሄደ ነው” አሉት።
27ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከላይ ካልተሰጠው በቀር ማንም አንዳች ሊቀበል አይችልም። 28‘እኔ ክርስቶስ#3፥28 ወይም መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ’ እንዳልሁ እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ። 29ሙሽራዪቱ የሙሽራው ነች፤ ድምፁን ለመስማት በአጠገቡ የሚቆመው ሚዜ ግን፣ የሙሽራውን ድምፅ ሲሰማ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ያ ደስታ የእኔ ነው፤ እርሱም አሁን ተፈጽሟል። 30እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል።
31“ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነው የምድር ነው፤ የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ 32ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን ምስክርነቱን ማንም አይቀበልም፤ 33ምስክርነቱንም የተቀበለ ሰው፣ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አረጋገጠ። 34እግዚአብሔር#3፥34 በግሪኩ እርሱ ይላል መንፈሱን ሳይሰፍር ስለሚሰጥ፣ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። 35አብ ወልድን ይወድዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል። 36በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።”#3፥36 አንዳንድ ተርጓሚዎች ትእምርተ ጥቅሱን ከ30 በኋላ ያደርጋሉ።
လက်ရှိရွေးချယ်ထားမှု
ዮሐንስ 3: NASV
အရောင်မှတ်ချက်
မျှဝေရန်
ကူးယူ
မိမိစက်ကိရိယာအားလုံးတွင် မိမိအရောင်ချယ်သောအရာများကို သိမ်းဆည်းထားလိုပါသလား။ စာရင်းသွင်းပါ (သို့) အကောင့်ဝင်လိုက်ပါ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.