ሉቃስ 14
14
ኢየሱስ በአንድ ፈሪሳዊ ቤት
14፥8-10 ተጓ ምብ – ምሳ 25፥6፡7
1አንድ ሰንበት ቀን፣ ኢየሱስ ምግብ ሊበላ ከፈሪሳውያን አለቆች አንዱ ወደ ነበረ ሰው ቤት በገባ ጊዜ፣ ሰዎች በዐይን ይከታተሉት ነበር። 2በዚያም በአካል ዕብጠት የሚሠቃይ አንድ ሰው ከፊት ለፊቱ ነበር። 3ኢየሱስም ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፣ “በሰንበት ቀን ሕመምተኞችን መፈወስ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?” ሲል ጠየቃቸው፤ 4እነርሱ ግን ዝም አሉ። እርሱም ሰውየውን ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው።
5ደግሞም፣ “ከእናንተ አንዱ፣ ልጁ#14፥5 አንዳንድ ቅጆች አህያው ይላሉ። ወይም በሬው በሰንበት ቀን ጕድጓድ ቢገባበት ፈጥኖ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው። 6እነርሱም ለዚህ አንዳች መልስ ሊያገኙ አልቻሉም።
7ኢየሱስ ተጋባዦቹ የክብር ስፍራ ሲመርጡ ተመልክቶ፣ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለእነርሱ ነገራቸው፤ 8“አንድ ሰው ሰርግ ቢጠራህ፣ በክብር ስፍራ አትቀመጥ፤ በክብር ከአንተ የሚበልጥ ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣ 9ሁለታችሁንም የጋበዘው መጥቶ፣ ስፍራውን ‘ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል፤ አንተም እያፈርህ ወደ ዝቅተኛው ስፍራ ትሄዳለህ። 10ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ ዝቅተኛውን ስፍራ አይተህ ተቀመጥ፤ ጋባዥህም ሲመጣ፣ ወዳጄ ሆይ፤ ወደ ላይ ከፍ በል ይልሃል፤ አንተም በዚያን ጊዜ አብረውህ በማእድ በተቀመጡ ሰዎች ሁሉ ፊት ትከበራለህ። 11ምክንያቱም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ራሱንም ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ከፍ ይላል።”
12ኢየሱስም የጋበዘውን ሰው ደግሞ እንዲህ አለው፤ “የምሳ ወይም የእራት ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ፣ በዐጸፋው እንዳይጋብዙህና ብድራትን እንዳይመልሱልህ፣ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ከበርቴ ጎረቤቶችህን አትጋብዝ። 13ነገር ግን ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስውሮችን ጥራ፤ 14ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል።”
የትልቅ ግብዣ ምሳሌነት
14፥16-24 ተጓ ምብ – ማቴ 22፥2-14
15ከኢየሱስ ጋር በማእድ ከተቀመጡት መካከል አንዱ ይህን ሰምቶ “በእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቦ ከማእድ የሚበላ ብፁዕ ነው” አለው።
16ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንድ ሰው ትልቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ብዙ ሰው ጠራ፤ 17የግብዣውም ሰዓት በደረሰ ጊዜ የተጋበዙትን እንግዶች፣ ‘እነሆ፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷልና ኑ’ ብሎ እንዲጠራ አገልጋዩን ላከባቸው።
18 “ነገር ግን ሁሉም የየራሳቸውን ምክንያት ይፈጥሩ ጀመር፤ አንደኛው፣ ‘ገና አሁን መሬት ስለ ገዛሁ ሄጄ ማየት አለብኝ፤ እባክህ፣ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለው።
19 “ሌላኛውም፣ ‘አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ እነርሱን ልፈትናቸው ስለሆነ እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ’ አለ።
20 “ሌላው ደግሞ፣ ‘ገና ሙሽራ ስለሆንሁ ልመጣ አልችልም’ አለ።
21 “አገልጋዩም ተመልሶ መጥቶ ይህንኑ ለጌታው ነገረው። በዚህን ጊዜ የቤቱ ጌታ ተቈጥቶ አገልጋዩን፣ ‘ቶሎ ብለህ ወደ ከተማው አውራ ጐዳናዎችና መተላለፊያ መንገዶች ውጣ፤ ድኾችንና አካለ ስንኩሎችን፣ ዐይነ ስውሮችንና ዐንካሶችን ወደዚህ አስገባቸው’ አለው።
22 “አገልጋዩም፣ ‘ጌታዬ፤ ያዘዝኸው ሁሉ ተፈጽሟል፤ ገና አሁንም ቦታ አለ’ አለው።
23 “ጌታውም አገልጋዩን፣ ‘ወደ ጐዳናዎችና ወደ ገጠር መንገዶች ውጣ፤ ቤቴም እንዲሞላ ያገኘኸውን ሁሉ በግድ አምጥተህ አስገባ፤ 24እላችኋለሁና ከተጋበዙት ከእነዚያ ሰዎች መካከል አንድ ሰው እንኳ ግብዣዬን አይቀምስም አለው።’ ”
ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከፍለው ዋጋ
25ብዙ ሕዝብ አብሮት እየተጓዙ ሳለ፣ ኢየሱስ ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፤ 26“ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱንና እናቱን ሚስቱንና ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፣ የራሱንም ሕይወት እንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፤ 27የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
28 “ከእናንተ አንድ ሰው ሕንጻ ለመሥራት ቢፈልግ፣ መደምደም መቻል አለመቻሉን በመጀመሪያ ተቀምጦ ዋጋውን የማይተምን ማነው? 29መሠረቱን ጥሎ መደምደም ቢያቅተው፣ ያዩት ሁሉ ይዘባበቱበታል፤ 30እንዲህም ይላሉ፤ ‘ይህ ሰው ማነጽ ጀምሮ ነበር፤ መደምደም ግን አቃተው።’
31 “ወይም አንድ ንጉሥ ከሌላው ንጉሥ ጋር ጦርነት ሊገጥም በሚነሣበት ጊዜ፣ ሃያ ሺሕ ሰራዊት አስከትቶ የሚመጣበትን ንጉሥ፣ በዐሥር ሺሕ ሰራዊት መመከት እንደሚችል ተቀምጦ የማይመክር ማን ነው? 32መቋቋም የማይችል ከሆነ፣ ሌላው ንጉሥ ገና ሩቅ ሳለ፣ መልእክተኞች ልኮ ዕርቅ ይጠይቃል። 33እንደዚሁም፣ ከእናንተ ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።
34 “ጨው መልካም ነው፤ ጨው ጣዕሙን ካጣ ግን እንዴት ተመልሶ የጨውነት ጣዕም ሊኖረው ይችላል? 35ለመሬትም ሆነ ለማዳበሪያነት የማይጠቅም በመሆኑ ወደ ውጭ ይጣላል።
“ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”
လက်ရှိရွေးချယ်ထားမှု
ሉቃስ 14: NASV
အရောင်မှတ်ချက်
မျှဝေရန်
ကူးယူ
မိမိစက်ကိရိယာအားလုံးတွင် မိမိအရောင်ချယ်သောအရာများကို သိမ်းဆည်းထားလိုပါသလား။ စာရင်းသွင်းပါ (သို့) အကောင့်ဝင်လိုက်ပါ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.