8
የዘሪው ምሳሌ
8፥4-15 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥2-23፤ ማር 4፥1-20
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ ዐለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ 2እንዲሁም ከርኩሳን መናፍስትና ከደዌ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች አብረውት ነበሩ፤ እነርሱም ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት የተባለችው ማርያም፣ 3የሄሮድስ ቤት ኀላፊ የነበረው የኩዛ ሚስት ዮሐና፣ ሶስና፣ ደግሞም ሌሎች ብዙዎች ነበሩ፤ እነዚህም በግል ንብረታቸው የሚያገለግሉት ነበሩ።
4ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰብስቦ ሳለ፣ ደግሞም ሰዎች ከተለያዩ ከተሞች ወደ እርሱ በሚጐርፉበት ጊዜ፣ ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ 5“አንድ ዐራሽ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ሲዘራም፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፣ በእግርም ተረጋገጠ፤ የሰማይ ወፎችም በሉት። 6አንዳንዱም ዘር በድንጋያማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ እንደ በቀለም ርጥበት አልነበረውምና ደረቀ። 7ሌላው ዘር ደግሞ እሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አብሮት አደገና ዐንቆ አስቀረው። 8ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ በበቀለም ጊዜ መቶ ዕጥፍ አፈራ።”
ይህን ብሎ ሲያበቃም ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።
9ደቀ መዛሙርቱም የዚህን ምሳሌ ትርጕም ጠየቁት። 10እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር ማወቅ ለእናንተ ተሰጥቷል፤ ለሌሎች ግን በምሳሌ እናገራለሁ፤ ይኸውም፣
“ ‘እያዩ ልብ እንዳይሉ፣
እየሰሙም እንዳያስተውሉ ነው።’
11 “እንግዲህ የምሳሌው ትርጕም ይህ ነው፤ ዘር የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። 12በመንገድ ዳር የወደቀው ቃሉን የሚሰሙ፣ ነገር ግን አምነው እንዳይድኑ ዲያብሎስ መጥቶ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። 13በድንጋያማ ቦታ ላይ የወደቀውም ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነዚህ ለጊዜው ያምናሉ እንጂ ሥር ስለሌላቸው በፈተና ጊዜ ፈጥነው የሚክዱ ናቸው። 14በእሾኽ መካከል የወደቀውም ቃሉን የሚሰሙት ናቸው፤ እነዚህም ውለው ዐድረው በምድራዊ ሕይወት ጭንቀት፣ በባለጠግነትና ተድላ ደስታ ታንቀው በሚገባ አያፈሩም። 15በመልካም መሬት ላይ የወደቀውም ቃሉን ቅንና በጎ በሆነ ልብ ሰምተው የሚጠብቁ፣ ታግሠውም በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
በመቅረዝ ላይ ያለ መብራት
16 “መብራትን አብርቶ ጋን ውስጥ ወይም በዐልጋ ሥር የሚያስቀምጥ ማንም የለም፤ ይልቁንም ወደ ቤት የሚገቡ ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጠዋል። 17የማይገለጥ የተሰወረ፣ የማይታወቅ ወደ ብርሃን የማይወጣ፣ የተደበቀ ነገር የለምና። 18እንግዲህ እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ፤ ላለው ይጨመርለታልና፤ ከሌለው ሁሉ ግን ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።”
የኢየሱስ እናትና ወንድሞች
8፥19-21 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥46-50፤ ማር 3፥31-35
19ከዚህ በኋላ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ እርሱ ወዳለበት መጡ፤ እነርሱም ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ሊቀርቡ አልቻሉም። 20በዚህ ጊዜ፣ “እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” የሚል ወሬ ደረሰው።
21እርሱም መልሶ፣ “እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት ናቸው” አላቸው።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ
8፥22-25 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥23-27፤ ማር 4፥36-41
8፥22-25 ተጓ ምብ – ማር 6፥47-52፤ ዮሐ 6፥16-21
22ከዕለታቱ በአንድ ቀን፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጀልባ ላይ ወጣ፤ ኢየሱስም፤ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው፤ ከዚያም ጕዞ ቀጠሉ። 23እየተጓዙ ሳሉም ኢየሱስ እንቅልፍ ወስዶት ተኛ፤ በዚህ ጊዜ በባሕሩ ላይ ማዕበል ተነሣ፤ ውሃውም ጀልባዋን ዘልቆ ስለ ገባ፣ አደጋ አፋፍ ላይ ደረሱ።
24ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፣ “ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ ማለቃችን እኮ ነው!” እያሉ ቀሰቀሱት።
እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውሃውን መናወጥ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱም ነውጡም ተወ፤ ጸጥታም ሆነ። 25እርሱም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እምነታችሁ የት አለ?” አላቸው።
እነርሱም በፍርሀትና በመደነቅ፣ “ይህ ነፋስንና ውሃን የሚያዝ፣ እነርሱም የሚታዘዙለት እርሱ ማን ነው?” ተባባሉ።
አጋንንት ያደረበት ሰው መፈወሱ
8፥26-37 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥28-34
8፥26-39 ተጓ ምብ – ማር 5፥1-20
26ከዚህ በኋላ ከገሊላ ባሻገር ወዳለው ወደ ጌርጌሴኖን#8፥26 አንዳንድ ቅጆች ጋድሬኔስ፣ ሌሎች ቅጆች ደግሞ ጌርጌ ሴኔስ ይላሉ፤ 37 ይመ አገር በጀልባ ተሻገሩ። 27ኢየሱስ ከጀልባዋ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ፣ አጋንንት ያደረበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ አገኘው፤ ይህ ሰው ለብዙ ጊዜ ልብስ ሳይለብስ፣ በቤትም ሳይኖር የመቃብርን ስፍራ ቤቱ ያደረገ ነበር። 28ኢየሱስንም ባየው ጊዜ እየጮኸ ፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ጋር ምን ጕዳይ አለህ? እንዳታሠቃየኝ እለምንሃለሁ” አለ። 29ርኩሱ#8፥29 ወይም ክፉ መንፈስ ይህን ያለው ከሰውየው እንዲወጣ ኢየሱስ አዝዞት ስለ ነበር ነው። ርኩሱ መንፈስ በየጊዜው ስለሚነሣበት ሰውየው በሰንሰለትና በእግር ብረት እየታሰረ ቢጠበቅም፣ የታሰረበትን ሰንሰለት እየበጣጠሰ ያደረበት ጋኔን ወደ በረሓ ይነዳው ነበር።
30ኢየሱስም፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
እርሱም ብዙ አጋንንት ገብተውበት ስለ ነበር፣ “ሌጌዎን” አለው። 31አጋንንቱም እንጦርጦስ ግቡ ብሎ እንዳያዝዛቸው አጥብቀው ለመኑት።
32በዚያም አካባቢ በተራራ ወገብ ላይ የብዙ ዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ አጋንንቱም ወደ ዐሣማው መንጋ ግቡ ብሎ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ እርሱም ፈቀደላቸው። 33አጋንንቱም ከሰውየው ወጥተው ወደ ዐሣማዎቹ ገቡ፤ የዐሣማውም መንጋ በገደሉ አፋፍ ቍልቍል በመንደርደር ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ሰጠመ።
34እረኞቹም የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ፣ ሸሽተው በመሄድ በከተማውና በገጠሩ አወሩ። 35ሕዝቡም የተደረገውን ነገር ለማየት ከያሉበት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶ፣ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በኢየሱስም እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ። 36በአጋንንት የተያዘው ሰው ሲድን ያዩትም፣ እንዴት እንደ ዳነ ለሕዝቡ አወሩላቸው። 37የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎችም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ስላደረባቸው፣ ከዚያ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ወደ ጀልባው ገብቶ ተመልሶ ሄደ።
38አጋንንት የወጡለትም ሰው አብሮት ለመሆን ኢየሱስን ለመነው፤ እርሱ ግን እንዲህ ሲል አሰናበተው፤ 39“ወደ ቤትህ ተመልሰህ፣ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላቅ ነገር ተናገር።” ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ታላቅ ነገር በከተማው ሁሉ በይፋ እየተናገረ ሄደ።
የሞተችው ልጅና የታመመችው ሴት
8፥40-56 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥18-26፤ ማር 5፥22-43
40ሕዝቡ ሁሉ መምጣቱን ይጠባበቁ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ በደስታ ተቀበሉት። 41በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵራብ አለቃ መጥቶ፣ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ለመነው፤ 42ይህን ልመና ያቀረበው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ አንዲት ልጅ ስለ ነበረችው ነው፤ እርሷ በሞት አፋፍ ላይ ነበረች።
ወደዚያው እያመራ ሳለ፣ ሕዝቡ በመጋፋት እጅግ ያጨናንቀው ነበር። 43ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ#8፥43 አያሌ ቅጆች ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ የሚለው የላቸውም። ሊፈውሳትም የቻለ ማንም አልነበረም። 44እርሷም ከበስተ ኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ይፈስስ የነበረው ደሟም ወዲያው ቆመ።
45ኢየሱስም፣ “የነካኝ ማነው?” አለ።
ሁሉም መንካታቸውን በካዱ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከብቦህ በግፊያ እያስጨነቀህ ነው” አለው።
46ኢየሱስ ግን፣ “አንድ ሰው ነክቶኛል፤ ኀይል ከእኔ እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አለ።
47ሴትዮዋም ሳትታወቅ መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ፣ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። 48እርሱም፣ “ልጄ ሆይ እምነትሽ ፈውሶሻል በሰላም ሂጂ” አላት።
49ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ፣ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታድክመው” አለው።
50ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፣ “አትፍራ፣ እመን ብቻ እንጂ፤ ልጅህ ትድናለች” አለው።
51ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲገባም ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቱ አባትና እናት በቀር ማንም አብሮት እንዲገባ አልፈቀደም። 52በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፣ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።
53ሰዎቹም መሞቷን ስላወቁ ሣቁበት። 54እርሱ ግን እጇን ይዞ፣ “ልጄ ሆይ፤ ተነሺ” አላት። 55የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሥታ ቆመች፤ ኢየሱስም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት አዘዛቸው። 56ወላጆቿም ተደነቁ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳያወሩ አዘዛቸው።