YouVersion लोगो
खोज आइकन

የሉቃስ ወንጌል 21

21
የመበለቲቱ መባ
(ማር. 12፥41-44)
1ዐይኑንም አንሥቶ በምጽዋት መቀበያ መባቸውን የሚያስቀምጡ ሀብታሞችን አየ። 2አንዲትም ድኻ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስታስቀምጥ አየና 3“እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ከሁሉ አብልጣ አስቀምጣለች፤ 4እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ መዝገቡ አስቀምጠዋልና፤ እርሷ ግን እየጐደላት የነበራትን ንብረት ሁሉ ሰጠች፤” አለ።
ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስ
(ማቴ. 24፥1-2ማር. 13፥1-2)
5አንዳንዶቹም ስለ ቤተ መቅደስ በመልካም ድንጋይና በተሰጠው ሽልማት እንዳጌጠ ሲነጋገሩ 6“ይህማ የምታዩት ሁሉ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ የማይቀርበት ዘመን ይመጣል፤” አለ።
የዘመኑ መጨረሻ ምልክቶችና ስደት
(ማቴ. 24፥3-14ማር. 13፥3-13)
7 # ማቴ. 24፥3-14፤ ማር. 13፥3-13። እነርሱም “መምህር ሆይ! እንግዲህ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሊሆን መቃረቡን የሚያሳየው ምልክቱ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት። 8እንዲህም አለ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች ‘እኔ ነኝ፤ ዘመኑም ቀርቦአል፤’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ እነርሱን ተከትላችሁ አትሂዱ። 9ጦርንና ሁከትንም በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ አስቀድሞ ይሆን ዘንድ ግድ ነውና፤ ነገር ግን መጨረሻው ወዲያው አይሆንም።”
10በዚያን ጊዜ እንዲህ አላቸው “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ 11ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ራብም ይሆናል፤ የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይታያል። 12ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ጭነው ይይዟችኋል፤ ያሳድዱአችኋ፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ 13ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል። 14#ሉቃ. 12፥11፤12።ሰለዚህም የመከላከያ መልስ አስቀድሞ ማዘጋጀት እንደማያስፈልጋችሁ ልብ በሉ። 15ተቃዋሚዎቻችሁ በሙሉ ሊቃወሙትና ሊከራከሩት የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና። 16ወላጆችና ወንድሞች፥ ዘመዶችና ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተም አንዳንዱን ይገድላሉ፤ 17በሁሉም ከስሜ የተነሣ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። 18ከራሳችሁም አንዲት ጠጉር ስንኳ አትጠፋም፤ 19በመታገሣችሁም ነፍሳችሁን ታተርፋላችሁ።
ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት
(ማቴ. 25፥15-21ማር. 13፥14-19)
20“ኢየሩሳሌም ግን በሠራዊት ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ። 21የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በመካከልዋም ያሉ ከእርሷ ይራቁ፤ በገጠር ያሉም ወደ እርሷ አይግቡ፤ 22#ሆሴዕ 9፥7።የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የቅጣት ጊዜ ነውና። 23በነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ታላቅ ችግር በምድር ላይ፥ በዚህም ሕዝብ ላይ ቁጣ ይሆናልና፤ 24በሰይፍ ስለትም ይወድቃሉ፤ ወደ አሕዛብ ሁሉ ይሰደዳሉ፤ የአሕዛብም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።
የሰው ልጅ ዳግመኛ መምጣት
(ማቴ. 24፥29-34ማር. 13፥24-27)
25 # ኢሳ. 13፥10፤ ሕዝ. 32፥7፤ ኢዩ. 2፥31፤ ራእ. 6፥12፤13። “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ላይ ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ በመረበሽ ይጨነቃሉ፤ 26የሰማያት ኀይላት ይናወጣሉና፥ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጣውን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ። 27#ዳን. 7፥13፤ ራእ. 1፥7።በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። 28ይህም መሆን ሲጀምር መዳናችሁ ቀርቦአልና ቁሙ፤ ቀናም በሉ።”
29እንዲህ ሲልም ምሳሌ ነገራቸው “በለስንና ዛፎችን ሁሉ እዩ፤ 30ሲያቈጠቁጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደ ቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 31እንዲሁ ደግሞ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ። 32እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 33ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።
34“ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር፥ ስለ ኑሮም ማሰብ እንዳይዝል፥ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ 35በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። 36እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ እየጸለያችሁ ሁልጊዜ ትጉ።”
37 # ሉቃ. 19፥47። ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሌሊት ግን ደብረዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር። 38ሕዝቡም ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው ወደ መቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።

अहिले सेलेक्ट गरिएको:

የሉቃስ ወንጌል 21: መቅካእኤ

हाइलाइट

शेयर गर्नुहोस्

कपी गर्नुहोस्

None

तपाईंका हाइलाइटहरू तपाईंका सबै यन्त्रहरूमा सुरक्षित गर्न चाहनुहुन्छ? साइन अप वा साइन इन गर्नुहोस्