Logoja YouVersion
Ikona e kërkimit

የሉቃስ ወንጌል 17

17
ስለ ማሰናከል እና ስለ ይቅርታ
(ማቴ. 18፥6-721-22ማር. 9፥42)
1ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “መሰናክል የግዱን ሳይመጣ አይቀርም፤ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤ 2ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር። 3#ማቴ. 18፥15።ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፤ ቢጸጸትም ይቅር በለው። 4በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ፥ በቀንም ሰባት ጊዜ ‘ተጸጸትሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው።”
5ሐዋርያትም ጌታን “እምነት ጨምርልን” አሉት። 6ጌታም አለ፦ “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል፤’ ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር።
7“ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ አገልጋይ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ ‘ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ፤’ የሚለው ማን ነው? 8‘የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፤ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ፤’ ይለው የለምን? 9ያዘዘውን ስላደረገ ያንን አገልጋይ ያመሰግነዋልን? 10እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ ‘የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል፤’ በሉ።”
ኢየሱስ ዐሥሩን ለምጻሞች እንደ አነጻ
11ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። 12ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት ዐሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ 13እነርሱም እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ! መምህር ሆይ! ማረን፤” አሉ። 14#ዘሌ. 14፥1-32።አይቶም “ሂዱ፤ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ፤” አላቸው። 15እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያወደሰ ተመለሰ፤ 16እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። 17ኢየሱስም መልሶ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? 18ከዚህ ከሌላ ወገን ሰው በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም፤” አለ። 19እርሱንም “ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል፤” አለው።
የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት
(ማቴ. 24፥23-2837-41)
20ፈሪሳውያንም “የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች?” ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ 21ደግሞም ‘ይችትና!’ ወይም ‘ያቻትና!’ የምትባል አይደለችም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና፤” አላቸው።
22ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች መካከል አንዱን ለማየት የምትመኙበት ወራት ይመጣል፤ አታዩትምም። 23እነርሱም ‘እነሆ በዚህ’ ወይም ‘እነሆ በዚያ’ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ፤ አትከተሉአቸውም። 24መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ አንድ ስፍራ ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ ስፍራ እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅም፥ በቀኑ፥ እንዲህ ይሆናል። 25አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ ሊቀበል፥ በዚህም ትውልድ ሊናቅ ይገባዋል። 26#ዘፍ. 6፥5-8።በኖኅ ዘመንም እንደሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመንም ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። 27#ዘፍ. 7፥6-24።ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፤ የጥፋት ውሃም መጣ፤ ሁሉንም አጠፋ። 28#ዘፍ. 18፥20—19፥25።እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ 29ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ፤ ሁሉንም አጠፋ። 30የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። 31#ማቴ. 24፥17፤18፤ ማር. 13፥15፤16።በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፤ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። 32#ዘፍ. 19፥26።የሎጥን ሚስት አስታውሱአት። 33#ማቴ. 10፥39፤ 16፥25፤ ማር. 8፥35፤ ሉቃ. 9፥24፤ ዮሐ. 12፥25።ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን የሚያጠፋ ሁሉ ይጠብቃታል። 34በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሁለተኛውም ይቀራል እላችኋለሁ። 35ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች፤ ሁለተኛይቱም ትቀራለች። 36ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሁለተኛውም ይቀራል።” 37ሲመልሱለትም “ጌታ ሆይ! ወዴት ነው?” አሉት። እርሱም “ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ፤” አላቸው።

Thekso

Ndaje

Copy

None

A doni që theksimet tuaja të jenë të ruajtura në të gjitha pajisjet që keni? Regjistrohu ose hyr