የዮሐንስ ወንጌል 6
6
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መመገቡ
(ማቴ. 14፥13-21፤ ማር. 6፥30-44፤ ሉቃ. 9፥10-17)
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጥብርያዶስ ወደሚባለው ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ። 2ብዙ ሰዎች ኢየሱስ በሽተኞችን በመፈወስ ያደረገውን ተአምር ስላዩ ተከተሉት። 3ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። 4የአይሁድ ፋሲካ በዓል ቀርቦ ነበር። 5በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ ቀና ብሎ አየና ፊልጶስን፦ “ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ ከየት መግዛት እንችላለን?” አለው። 6ኢየሱስ ይህን የተናገረው ፊልጶስን ለመፈተን ነበር እንጂ፥ የሚያደርገውንስ እርሱ ራሱ ያውቅ ነበር።
7ፊልጶስም “ለእያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ ቊራሽ እንኳ እንዲሰጣቸው የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም” ሲል መለሰለት። #6፥7 ዲናር፦ የቀን ሠራተኛ የአንድ ቀን ደመወዝ ነው።
8ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለ፦ 9“አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ እዚህ አለ፤ ነገር ግን ይህ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምን ይበቃል?” 10ኢየሱስም “ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉአቸው” አለ። በዚያ ቦታ ብዙ ሣር ነበረ፤ ሰዎቹም ተቀመጡ፤ ቊጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያኽል ነበር። 11ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንጀራውን አንሥቶ ምስጋና ካቀረበ በኋላ ለተቀመጡት ሰዎች ዐደላቸው። እንዲሁም ዓሣዎቹን አከፋፈላቸው፤ ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ያኽል አገኙ። 12ሁሉም በልተው ከጠገቡ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “አንድም ነገር እንዳይባክን የተረፈውንም ፍርፋሪ ሰብስቡ” አላቸው። 13እነርሱም ሰዎቹ በልተው ከተረፈው ከአምስቱ የገብስ እንጀራ ፍርፋሪውን ሰብስበው በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።
14ሰዎቹም ኢየሱስ ያደረገውን ተአምር ባዩ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው!” አሉ። 15ሰዎቹ ግን በግድ ወስደው ሊያነግሡት እንዳሰቡ ባወቀ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን እንደገና ራቅ ብሎ ወደ ኮረብታ ሄደ።
ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ እንደ ሄደ
(ማቴ. 14፥22-33፤ ማር. 6፥45-52)
16በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ። 17በጀልባ ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም አመሩ፤ በዚያን ሰዓት ጊዜው ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር። 18ኀይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለ ነበር፤ ባሕሩ ተናወጠ። 19ደቀ መዛሙርቱ አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ያኽል እየቀዘፉ ከተጓዙ በኋላ ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲቀርብ አይተው ፈሩ። 20እርሱ ግን “እኔ ነኝ! አትፍሩ!” አላቸው። 21እነርሱም በደስታ ተቀብለው ወደ ጀልባዋ ሊያስገቡት ፈለጉ፤ ወዲያውኑ ጀልባዋ ወደሚሄዱበት ቦታ ደረሰች።
ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ መሆኑ
22በማግስቱ ከባሕሩ ማዶ ቀርተው የነበሩት ሰዎች፥ በባሕሩ ላይ አንድ ጀልባ ብቻ እንደ ነበረና በዚያም ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን እንደ ሄዱ፥ ኢየሱስ ግን ከእነርሱ ጋር ወደ ጀልባዋ እንዳልገባ አይተው ነበር። 23ሆኖም ሌሎች ጀልባዎች ከጥብርያዶስ ተነሥተው ኢየሱስ የምስጋና ጸሎት ወደአደረገበትና ሕዝቡ እንጀራ ወደ በላበት ስፍራ አጠገብ መጡ። 24ሰዎቹም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በእዚያ እንደሌሉ ባዩ ጊዜ በነዚያ ጀልባዎች ተሳፍረው ኢየሱስን ፍለጋ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ። 25ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፥ “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት።
26ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስላያችሁ አይደለም። 27ለሚጠፋ ምግብ አትሥሩ፤ ይልቅስ እግዚአብሔር አብ የማረጋገጫ ማኅተም ስለ አተመው የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ፥ የዘለዓለም ሕይወት ለሚሆነው ምግብ ሥሩ።”
28ሰዎቹም “ታዲያ፥ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ ይገባናል?” አሉት።
29ኢየሱስም “የእግዚአብሔር ሥራማ እግዚአብሔር በላከው ማመን ነው” ሲል መለሰላቸው።
30እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “እኛ አይተን በአንተ እንድናምን ምን ተአምር ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ? 31‘እንዲበሉ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ አባቶቻችን በበረሓ መና በልተዋል።” #ዘፀ. 16፥4፤15፤ መዝ. 78፥24።
32በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከሰማይ የወረደውን እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው፤ 33የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድና ለዓለም ሕይወትን የሚሰጥ ነው።” 34ስለዚህ ሰዎቹ “ጌታ ሆይ! ይህን ዐይነት እንጀራ ዘወትር ስጠን” አሉት።
35ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ፈጽሞ አይራብም፤ በእኔ የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም፤ 36እናንተ ግን አይታችሁኛል፤ ግን በእኔ አላመናችሁም እላችኋለሁ። 37አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ፈጽሞ ወደ ውጪ አላባርረውም። 38እኔ ከሰማይ የወረድኩት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም። 39የላከኝ ፈቃድ፥ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳላጠፋ በመጨረሻው ቀን ከሞት እንዳስነሣቸው ነው። 40አዎ! የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያይና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ።” 41ስለዚህ ኢየሱስ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ አይሁድ በእርሱ ላይ አጒረመረሙ፤ 42እንዲህም አሉ፦ “ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱንስ እናውቃቸው የለምን? ታዲያ፥ አሁን እርሱ እንዴት ‘ከሰማይ ወረድኩ’ ይላል?”
43ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤ 44የላከኝ አብ የሳበው ካልሆነ በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል ማንም የለም፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም በመጨረሻ ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ። 45በነቢያት መጻሕፍት ‘ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ ስለዚህ ከአብ ሰምቶ የተማረ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል። #ኢሳ. 54፥13። 46ይህም ማለት አብን ያየው ሰው አለ ማለት አይደለም፤ አብን ያየው ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣው እርሱ ብቻ ነው። 47እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ (በእኔ) የሚያምን ሰው የዘለዓለም ሕይወት አለው። 48እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፤ 49አባቶቻችሁ በበረሓ መና በሉ፤ ነገር ግን ሞቱ፤ 50ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ ይህን እንጀራ የሚበላ በፍጹም አይሞትም። 51ከሰማይ የወረደው ሕይወትን የሚሰጥ እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ሁሉ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን እኔ የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።”
52በዚህ ጊዜ አይሁድ “ይህ ሰው ሥጋውን እንድንበላ እንዴት ሊሰጠን ይችላል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።
53ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላና ደሜንም የሚጠጣ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን ከሞት አስነሣዋለሁ። 55ሥጋዬ እውነተኛ መብል፥ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው። 56ሥጋዬን የሚበላና ደሜን የሚጠጣ ሁሉ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57ሕያው አብ እንደ ላከኝና እኔም በእርሱ ሕያው እንደ ሆንኩ እንዲሁም ሥጋዬን የሚበላ ሁሉ በእኔ ሕያው ይሆናል። 58እንግዲህ ከሰማይ የወረደው እንጀራ ይህ ነው፤ እርሱም አባቶቻችሁ እንደ በሉት ዐይነት አይደለም፤ ያን እንጀራ የበሉ ሞተዋል፤ ይህን እንጀራ የሚበሉ ግን ዘለዓለም ይኖራሉ።”
59ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም በምኲራብ በሚያስተምርበት ጊዜ ነበር።
የዘለዓለም ሕይወት ቃል
60ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ “ይህ አነጋገር ከባድ ነው፤ ማን ሊቀበለው ይችላል?” አሉ።
61ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንዳጒረመረሙ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ነገር ያሰናክላችኋልን? 62የሰው ልጅ ወደነበረበት ተመልሶ ሲወጣ ስታዩ ምን ልትሉ ነው? 63ሕይወትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሰው ኀይል ግን ለምንም አይጠቅምም፤ እኔ ለእናንተ የተናገርኩት ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው፤ 64ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዳንዶች የማያምኑ አሉ፤” ኢየሱስ ይህን የተናገረው ከመጀመሪያ አንሥቶ የማያምኑ እነማን እንደ ነበሩና አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። 65ቀጥሎም ኢየሱስ “ከአብ የተፈቀደለት ካልሆነ በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚችል የለም ያልኳችሁ ስለዚህ ነው” አለ።
66በዚህም ምክንያት ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኢየሱስን መከተል ተዉ። 67ስለዚህ ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት፥ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። 68በዚህ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘለዓለም ሕይወት ቃል አለህ። 69እኛስ አምነናል፤ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ አንተ እንደ ሆንክም ዐውቀናል።” #ማቴ. 16፥16፤ ማር. 8፥29፤ ሉቃ. 9፥20። 70ኢየሱስም “እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን መርጬአችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው። 71ይህንንም ያለው ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮታዊው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ምንም እንኳ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ቢሆን ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ስለ ነበር ነው።
Iliyochaguliwa sasa
የዮሐንስ ወንጌል 6: አማ05
Kuonyesha
Shirikisha
Nakili
Je, ungependa vivutio vyako vihifadhiwe kwenye vifaa vyako vyote? Jisajili au ingia
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997