የዮሐንስ ወንጌል 6
6
ወደ ጥብርያዶስ ስለ መሄዱ
1ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ወደ ጥብርያዶስ ሄደ። 2በበሽተኞችም ላይ ያደረገውን ተአምራት ስለ አዩ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ 3ጌታችን ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣ፤ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር በዚያ ተቀመጠ። 4የአይሁድ የፋሲካ በዓልም ቀርቦ ነበር።
አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ስለ ማበርከቱ
5ጌታችን ኢየሱስም ዐይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ሲመጡ አየና ፊልጶስን፥ “ለእነዚህ ሰዎች የምናበላቸው እንጀራ ከወዴት እንግዛ?” አለው። 6ሲፈትነው ይህን አለ እንጂ፥ እርሱስ የሚያደርገውን ያውቅ ነበር። 7ፊልጶስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “ከእነርሱ ለእያንዳንዱ ጥቂት ጥቂት ይወስዱ ዘንድ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም።” 8ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ እንዲህ አለው፥ 9“አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህ ይህን ለሚያህል ሰው ምን ይበቃሉ?” 10ጌታችን ኢየሱስም፥ “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ” አለ፤ የዚያ ቦታም ሣሩ ብዙ ነበር፤ ወንዶቹም በመስኩ ላይ ተቀመጡ፤ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ ያህል ነበር። 11ጌታችን ኢየሱስም ያን እንጀራ ይዞ አመሰገነ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው፤#“ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰጡአቸው” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። ከዓሣውም እንዲሁ የፈለጉትን ያህል ሰጡአቸው። 12ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ከቍርስራሹ ምንም የሚወድቅ እንዳይኖር የተረፈውን ቍርስራሽ አንሡ፤” አላቸው። 13እነርሱም ሰበሰቡ፥ በልተው ከጠገቡ በኋላም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈው ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሞላ። 14ሕዝቡም ጌታችን ኢየሱስ ያደረገውን ተአምራት አይተው፥ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው” አሉ። 15ጌታችን ኢየሱስም መጥተው ነጥቀው ሊያነግሡት እንደሚሹ ዐወቀባቸውና ብቻውን ወደ ተራራ ሄደ።
በባሕር ላይ ስለ መሄዱ
16በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ። 17ወደ ታንኳም ወጡ፤ ወደ ባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆምም ሄዱ፤ እነሆም፥ ፈጽሞ ጨለማ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ እነርሱ ገና አልመጣም ነበር። 18ባሕሩ ግን ይታወክ ነበር፤ ጽኑ ነፋስ ይነፍስ ነበርና። 19ሃያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ያህል ከሄዱ በኋላ ጌታችን ኢየሱስን በባሕር ላይ ሲሄድ አዩት፤ ወደ ታንኳዉ በቀረበ ጊዜም ፈሩ። 20እርሱም፥ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው። 21ወደ ታንኳውዪቱ ሊያወጡት ሲሹም ታንኳዪቱ ወዲያውኑ ሊሄዱ ወደ ወደዱበት ወደብ ደረሰች። 22በማግሥቱም ከባሕሩ ዳር ቆመው የነበሩ ሰዎች ከአንዲት ታንኳ በቀር ከዚያ ሌላ ታንኳ እንዳልነበረ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ሄዱ እንጂ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ እንዳልወጣ አዩ። 23ደግሞም ጌታችን የባረከውን እንጀራ ከበሉበት ቦታ አቅራቢያ ከጥብርያዶስ ሌሎች ታንኳዎች መጥተው ነበር። 24እነዚያ ሰዎችም ጌታችን ኢየሱስ፥ ደቀ መዛሙርቱም በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስን ይፈልጉት ዘንድ በእነዚያ ታንኳዎች ገብተው ወደ ቅፍርናሆም መጡ። 25በባሕሩ ዳርም ባገኙት ጊዜ፥ “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት።
ስለ ሕይወት ምግብ
26ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስለ አያችሁ አይደለም። 27የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤ ይህን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” 28“እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሥራ እንሠራ ዘንድ ምን እናድርግ?” አሉት። 29ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ ነው፤” አላቸው።
ምልክት ስለ መጠየቃቸው
30እነርሱም እንዲህ አሉት፥ “የምትሠራውን አይተን በአንተ እናምን ዘንድ ምን ተአምራት ታደርጋለህ? 31#ዘፀ. 16፥4፤ 15፤ መዝ. 77፥24። አባቶቻችንስ ‘ሊበሉ እንጀራ ከሰማይ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ በምድረ በዳ መና በሉ። 32ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ያን እንጀራ ከሰማይ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ከሰማይ የእውነት እንጀራን ሰጥቶአችኋል እንጂ። 33የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ፤ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።” 34እነርሱም፥ “አቤቱ ከዚያ እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን” አሉት።
ስለ ሕይወት ኅብስት
35ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምንም ለዘለዓለም አይጠማም። 36ነገር ግን እላችኋለሁ፤ አያችሁኝ፤ አላመናችሁብኝምም። 37አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም። 38ከሰማይ የወረድሁ የላከኝን ፈቃድ እንጂ፥ ፈቃዴን ላደርግ አይደለምና። 39የላከኝ የአብ ፈቃድም ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድስ እንኳ ቢሆን እንዳይጠፋ ነው፤ ነገር ግን እኔ በኋለኛዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ። 40የአባቴ ፈቃዱ ይህ ነው፤ ወልድን አይቶ የሚያምንበት ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ።”
ስለ አይሁድ ማንጐራጐር
41አይሁድም ስለ እርሱ አንጐራጐሩ፤ “ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ብሎአቸዋልና። 42“እኛ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል?” አሉ። 43ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። 44የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ መምጣትን የሚችል የለም፤ እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ። 45#ኢሳ. 54፥13። ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ በነቢያት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአባቴ የሰማ ሁሉ ተምሮ ወደ እኔ ይመጣል። 46ከእግዚአብሔር ከሆነው በቀር አብን ያየው ማንም የለም፤ እርሱም አብን አየው። 47እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው። 48የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። 49አባቶቻችሁስ በምድረ በዳ መና በሉ፥ ሞቱም። 50ከእርሱ የበላ ሁሉ እንዳይሞት ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው።”
ስለ ሥጋውና ስለ ደሙ
51“ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው ይህ እንጀራ ሥጋዬ ነው።”
52አይሁድም፥ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። 53ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ፥ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም። 54ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛዪቱ ቀን አነሣዋለሁ። 55ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነውና፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። 56ሥጋዬን የሚበላ፥ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ። 57የላከኝ አብ ሕያው እንደ ሆነ፥ እኔም ስለ አብ ሕያው ነኝ፤ ሥጋዬንም የሚበላ እርሱ ደግሞ ስለ እኔ ሕያው ሆኖ ይኖራል። 58ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ በልተውት እንደሞቱበት ያለ መና አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል።” 59በቅፍርናሆምም በምኵራብ ሲያስተምራቸው ይህን ተናገረ፤
ስለ ተጠራጠሩት ሰዎች
60ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎቹ ይህን ሰምተው፥ “ይህ ነገር የሚያስጨንቅ ነው፤ ማንስ ሊሰማው ይችላል?” አሉ። 61ጌታችን ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ አንጐራጐሩ በልቡ ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ያሰናክላችኋልን? 62እንግዲህ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሲያርግ ብታዩት እንዴት ይሆን? 63ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ግን አንዳች አይጠቅምም፤ ይህም እኔ የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው። 64ነገር ግን ከእናንተ ውስጥ የማያምኑ አሉ፤” ጌታችን ኢየሱስ ከጥንት ጀምሮ የማያምኑበት እነማን እንደ ሆኑ፥ የሚያሲዘውም ማን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና። 65እንዲህም አላቸው፥ “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ከአብ ካልተሰጠው በቀር ወደ እኔ መምጣት የሚቻለው የለም።”
66ስለዚህም ከደቀ መዛሙርቱ ወደ ኋላቸው የተመለሱ ብዙዎች ናቸው፤ ከዚያም ወዲህ አብረውት አልሄዱም። 67ጌታችን ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፥ “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትሻላችሁን?” አላቸው። 68ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “አቤቱ፥ የዘለዓለም የሕይወት ቃል እያለህ ወደ ማን እንሄዳለን? 69#ማቴ. 16፥16፤ ማር. 8፥29፤ ሉቃ. 9፥20። እኛስ የሕያው#ግሪኩ እና አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ቅዱስ” ይላል። እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንደ ሆንህ አምነናል፤ አውቀናልም።” 70ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እኔ እናንተን ዐሥራ ሁለታችሁን መርጫችሁ የለምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ሰይጣን ነው።” 71ይህንም ስለ ስምዖን ልጅ ስለ አስቆሮታዊው ይሁዳ ተናገረ፤ እርሱ ያሲዘው ዘንድ አለውና፤ እርሱም ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ነበር።
Поточний вибір:
የዮሐንስ ወንጌል 6: አማ2000
Позначайте
Поділитись
Копіювати
Хочете, щоб ваші позначення зберігалися на всіх ваших пристроях? Зареєструйтеся або увійдіть