ዮሐንስ 11
11
የአልዓዛር መሞት
1በማርያምና በእኅቷ በማርታ መንደር በቢታንያ ይኖር የነበረው አልዓዛር ታሞ ነበር። 2ይህች ወንድሟ አልዓዛር የታመመባት ማርያም፣ በጌታ ላይ ሽቱ አፍስሳ እግሩን በጠጕሯ ያበሰችው ነበረች። 3እኅትማማቾቹም፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትወድደው ሰው ታምሟል” ብለው መልእክት ላኩበት።
4ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ “ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት የሚያደርስ አይደለም” አለ። 5ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወድዳቸው ነበር። 6ሆኖም አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ፣ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ቈየ።
7ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው።
8እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩህ እየፈለጉህ ነበር፤ እንደ ገና ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት።
9ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ብርሃን አይደለምን? ከዚህ ዓለም ብርሃን የተነሣ ስለሚያይ በቀን የሚመላለስ አይሰናከልም፤ 10የሚሰናከለው ግን በሌሊት የሚመላለስ ነው፤ ብርሃን የለውምና።”
11ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው።
12ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል” አሉት። 13ኢየሱስ ይህን የነገራቸው ስለ ሞቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ መሰላቸው።
14ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ “አልዓዛር ሞቷል፤ 15ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ባለ መኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።”
16ከዚያም ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ሄደን ከእርሱ ጋር እንሙት” አላቸው።
ኢየሱስ የአልዓዛርን እኅቶች ማጽናናቱ
17ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር። 18ቢታንያ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ#11፥18 ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ነው። ያህል ትርቅ ነበር። 19ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤ 20ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር።
21ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር። 22አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።”
23ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት።
24ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው።
25ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ 26በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?”
27እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ#11፥27 ወይም መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው።
28ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት። 29ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። 30በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። 31ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሏቸው ተከተሏት።
32ማርያምም ኢየሱስ ወደ ነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው።
33ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በሐዘን ታውኮ፣ 34“የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ።
እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት።
35ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።
36አይሁድም፣ “እንዴት ይወድደው እንደ ነበር አያችሁ” አሉ።
37ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዐይነ ስውሩን ዐይን የከፈተ፣ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ።
ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ
38ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በሐዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤ 39እርሱም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ።
የሟቹም እኅት ማርታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” አለችው።
40ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” አላት።
41ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ 42ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።”
43ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ። 44የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ።
ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው።
ኢየሱስን ለመግደል የተደረገ ሤራ
45ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፣ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩት አይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ። 46አንዳንዶቹ ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ለፈሪሳውያን ተናገሩ፤ 47ከዚያም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ።
እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? 48እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ስፍራችንንና#11፥48 ወይም መቅደሳችንን ሕዝባችንን ይወስዱብናል።”
49ከመካከላቸውም አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እናንተ እኮ ምንም አታውቁም! 50ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።”
51ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤ 52ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው። 53ከዚያን ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ።
54ስለዚህ ኢየሱስ ከዚያ ወዲያ በአይሁድ መካከል በይፋ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን በምድረ በዳ አጠገብ ወደምትገኝ ኤፍሬም ወደ ተባለች መንደር ገለል አለ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሰነበተ።
55የአይሁድ ፋሲካ እንደ ተቃረበም፣ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የመንጻት ሥርዐት ለማድረግ ብዙዎች ከአገር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 56ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው፣ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓሉ አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ። 57የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን ይይዙት ዘንድ የት እንዳለ የሚያውቅ ሰው እንዲጠቍም ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።
Đang chọn:
ዮሐንስ 11: NASV
Tô màu
Chia sẻ
Sao chép
Bạn muốn lưu những tô màu trên tất cả các thiết bị của mình? Đăng ký hoặc đăng nhập
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.