ኦሪት ዘፍጥረት 13
13
የአብራምና ሎጥ መለያየት
1አብራምም ከግብፅ ወጣ፤ እርሱና ሚስቱ፥ ለእርሱ የነበረውም ሁሉ፥ ሎጥም ከእርሱ ጋር ወደ አዜብ ወጡ። 2አብራምም በከብት፥ በብርና በወርቅ እጅግ በለጸገ። 3ከአዜብ ባደረገው በጕዞውም ወደ ቤቴል ሄደ፤ ያም ስፍራ አስቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳን ተክሎበት የነበረው ነው፤ 4ስፍራውም አስቀድሞ መሠውያ የሠራበት ነው፤ በዚያም አብራም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። 5ከአብራም ጋር የሄደው ሎጥ ደግሞ የላምና የበግ መንጋ ድንኳኖችም ነበሩት። 6በአንድነትም ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው ብዙ ነበርና፤ ስለዚህም ባንድነት ይቀመጡ ዘንድ ምድር አልበቃቻቸውም። 7በአብራምና በሎጥ መንጎች ጠባቆች መካከልም ጠብ ሆነ፤ በዚያ ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያች ምድር ተቀምጠው ነበር። 8አብራምም ሎጥን አለው፥ “እኛ ወንድማማች ነንና በእኔና በአንተ፥ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ አይሁን። 9እነሆ፥ ምድር ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ አንተ ወደ ግራው ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተም ወደ ቀኙ ብትሄድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።” 10ሎጥም ዓይኖቹን አነሣ፤ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውንም ሀገር ሁሉ ውኃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ አስቀድሞ እስከ ሴጎር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነትና እንደ ግብፅ ምድር እንደ ነበረ አየ። 11ሎጥም ለራሱ በዮርዳኖስ ዙሪያ ያለውን ሀገር ሁሉ መረጠ፤ ሎጥም ወደ ምሥራቅ ተጓዘ፤ አንዱም ከሌላው እርስ በርሳቸው ተለያዩ። 12አብራም በከነዓን ምድር ተቀመጠ፤ ሎጥም በጎረቤት ሕዝቦች ከተማ ተቀመጠ፤ ድንኳኑንም በሰዶም ተከለ፤#ግእዙ “ወደ ሰዶም ተጓዘ” ይላል። 13የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኀጢአተኞች ነበሩ።
አብራም ወደ ኬብሮን እንደ ሄደ
14ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው፥ “ዐይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ መስዕና ወደ አዜብ፥ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ 15የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘለዓለም እሰጣለሁና። 16ዘርህንም እንደ ባሕር አሸዋ#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “እንደ ምድር አሸዋ” ይላል። አደርጋለሁ፤ የባሕር አሸዋን ይቈጥር ዘንድ የሚችል ሰው ቢኖር ዘርህ ደግሞ ይቈጠራል። 17ተነሣ፤ በምድር በርዝመቷም፥ በስፋቷም ዙር፤ እርስዋን ለአንተና ለዘርህ ለዘለዓለም እሰጣለሁና።” 18አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ መጥቶም በኬብሮን ባለው የመምሬ ዛፍ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 13: አማ2000
Qaqambisa
Share
Copy
Ufuna ukuba iimbalasane zakho zigcinwe kuzo zonke izixhobo zakho? Bhalisela okanye ngena