ገለዓዳውያን ወደ ኤፍሬም የሚያሻግሩትን የዮርዳኖስን መልካዎች ያዙ። ታዲያ አምልጦ የሚሸሽ አንድ ኤፍሬማዊ ለመሻገር በሚጠይቃቸው ጊዜ፣ የገለዓድ ሰዎች “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ ያም ሰው፣ “አይደለሁም” ብሎ ከመለሰላቸው፣ እስኪ “ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ ቃሉን በትክክል ማለት ሳይችል ቀርቶ “ሲቦሊት” ካለ፣ ይዘው እዚያው እመልካው ላይ ይገድሉታል። በዚያ ጊዜም አርባ ሁለት ሺሕ ኤፍሬማውያን ተገደሉ።