1 ሳሙኤል 31

31
የሳኦል መሞት
31፥1-13 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 1፥4-121ዜና 10፥1-12
1በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያንም ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ። 2ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው አሳደዷቸው፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ። 3ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው ክፉኛ አቈሰሉት።
4ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ሸለፈታሞች መጥተው መሣለቂያ እንዳያደርጉኝ፣ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ” አለው።
ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፣ ፈቃደኛ አልሆነም። ስለዚህ ሳኦል በገዛ ሰይፉ ላይ ወድቆ ሞተ። 5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ፣ እርሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ዐብሮት ሞተ። 6ሳኦልና ሦስት ልጆቹ፣ ዐብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በአንድ ላይ በዚያ ቀን ነበር።
7በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን፣ የእስራኤል ሰራዊት መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ሲያዩ፣ ከተሞቻቸውን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።
8በማግስቱ ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9ከዚያም የሳኦልን ራስ ቈርጠው፣ የጦር መሣሪያውንም ገፍፈው፣ ለቤተ ጣዖቶቻቸውና ለሕዝቡ የምሥራቹን እንዲናገሩ ወደ መላው የፍልስጥኤም ምድር መልክተኞችን ላኩ። 10የጦር መሣሪያውን በአስታሮት ቤተ ጣዖት ውስጥ አስቀመጡት፤ ሬሳውን ደግሞ በቤትሳን ግንብ ላይ አንጠለጠሉት።
11የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣ 12ጀግኖቻቸው ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሙሉ ተጓዙ፤ የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ ከቤትሳን ግንብ ላይ አውርደው ወደ ኢያቢስ አምጥተው አቃጠሉ። 13ከዚያም ዐጥንቶቻቸውን ወስደው በኢያቢስ ባለው የአጣጥ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ።

Currently Selected:

1 ሳሙኤል 31: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ