የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ጢሞቴዎስ 1

1
1በክርስቶስ ኢየሱስ ቃል በተገባው የሕይወት ተስፋ መሠረት፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፤
2ለተወዳጁ ልጄ፣ ለጢሞቴዎስ፤
ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ይሁን።
ታማኝ ስለ መሆን የተሰጠ ማበረታቻ
3ሳላቋርጥ ሌሊትና ቀን በጸሎቴ ስለ አንተ ሳስብ፣ ቀደምት አባቶች እንዳደረጉት በንጹሕ ኅሊና የማመልከውን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። 4እንባህን እያስታወስሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ። 5ግብዝነት የሌለበት እምነትህን አስታውሳለሁ፤ ይህ እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ እንዲሁም በእናትህ በኤውንቄ ዘንድ ነበረ፤ አሁን ደግሞ በአንተ እንዳለ ተረድቻለሁ።
6ስለዚህ በእጆቼ መጫን የተቀበልኸውን በአንተ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታቀጣጥል አሳስብሃለሁ። 7እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንምና። 8እንግዲህ፣ ስለ ጌታችን ለመመስከር ወይም የርሱ እስረኛ በሆንሁት በእኔ አትፈር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ስለ ወንጌል ከእኔ ጋራ መከራን ተቀበል። 9እኛ ስላደረግነው አንዳች ነገር ሳይሆን፣ ከዕቅዱና ከጸጋው የተነሣ ያዳነን፣ ወደ ቅዱስ ሕይወትም የጠራን እርሱ ነው። ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤ 10አሁን ግን ሞትን ደምስሶ በወንጌል አማካይነት ሕይወትንና ኢመዋቲነትን ወደ ብርሃን ባወጣው በመድኀኒታችን በክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ተገልጧል። 11እኔም ለዚህ ወንጌል የምሥራች ነጋሪና ሐዋርያ፣ አስተማሪም ሆኜ ተሾምሁ። 12መከራን የምቀበለውም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም ያመንሁትን እርሱን ስለማውቅ አላፍርበትም፤ የሰጠሁትንም ዐደራ እስከዚያች ቀን ድረስ መጠበቅ እንደሚችል ተረድቻለሁ።
13ከእኔ የሰማኸውን የጤናማ ትምህርት ምሳሌ አድርገህ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር ያዝ። 14የተሰጠህን መልካሙን ዐደራ በእኛ ውስጥ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ።
ታማኝ የመሆንና ያለመሆን ምሳሌዎች
15በእስያ አውራጃ ያሉት ሁሉ እንደ ተዉኝ ታውቃለህ፤ ከእነርሱም መካከል ፊሎጎስና ሄርዋጌኔስ ይገኛሉ።
16ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ቸርነት አድርጎልኛል፤ በታሰርሁበትም ሰንሰለት አላፈረም። 17እንዲያውም ወደ ሮም በመጣ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ። 18በዚያች ቀን ምሕረትን ከጌታ ያገኝ ዘንድ ጌታ ይስጠው፤ በኤፌሶንም የቱን ያህል እንዳገለገለኝ አንተ በሚገባ ታውቃለህ።

Currently Selected:

2 ጢሞቴዎስ 1: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ