የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 16

16
ፋሲካ
16፥1-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20ዘሌ 23፥4-8ዘኍ 28፥16-25
1አምላክህ እግዚአብሔር በአቢብ ወር ከግብጽ በሌሊት ስላወጣህ፣ የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብርበት። 2እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋህ አንዱን እንስሳ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርገህ ሠዋው። 3እርሾ ያለበት ቂጣ አትብላ፤ ከግብጽ የወጣኸው በችኰላ ነውና ከግብጽ የወጣህበትን ጊዜ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ታስብ ዘንድ እርሾ የሌለበት ቂጣ ሰባት ቀን ብላ። 4በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማንኛውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቈይ አታድርግ።
5አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤ 6ነገር ግን ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ፣ ፀሓይ ስትጠልቅ ምሽቱ#16፥6 ወይም፣ ፀሓይ ስትወጣ ንጋቱ ላይ። ላይ ከግብጽ በወጣህበት ሰዓት#16፥6 ወይም ዓመታዊ መታሰቢያ እንዲሆን፣ በዚያ ፋሲካን ሠዋ። 7ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ እግዚአብሔር በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ። 8ለስድስት ቀን እርሾ የሌለበት ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ጉባኤ አድርግ፤ ሥራም አትሥራበት።
የመከር በዓል
16፥9-12 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥15-22ዘኍ 28፥26-31
9እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቍጠር። 10ከዚያም በኋላ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን፣ የእጅህን የበጎ ፈቃድ ስጦታ በማቅረብ የሰባቱ ሱባዔ የመከር በዓል አምላክህን እግዚአብሔርን አክብር። 11አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፣ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች አምላክህ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 12አንተም በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህንም በጥንቃቄ ጠብቅ።
የዳስ በዓል
16፥13-17 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥33-43ዘኍ 29፥12-39
13የእህልህን ምርት ከዐውድማህ፣ ወይንህንም ከመጭመቂያህ ከሰበሰብህ በኋላ፣ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብር። 14በበዓልህ አንተ፣ ወንድና ሴት ልጅህ፣ ወንድና ሴት አገልጋይህ፣ በከተማው ያለ ሌዋዊ፣ መጻተኛ፣ አባት አልባውና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ። 15እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በዓሉን ሰባት ቀን አክብር፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእህል ምርትህና በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክሃል፤ ደስታህም ፍጹም ይሆናል።
16ወንዶችህ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ፣ በቂጣ በዓል፣ በሰባቱ ሱባዔ የመከር በዓልና በዳስ በዓል ላይ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረቡ፤ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጁን አይቅረብ። 17አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን እያንዳንዱ ይስጥ።
ስለ ፍርድ አሰጣጥ
18አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ከተሞች ሁሉ ለየነገዶችህ ዳኞችንና አለቆችን ሹም፤ እነርሱም ሕዝቡን በጽድቅ ፍርድ ይዳኙ። 19ፍርድ አታዛባ፤ አድልዎ አታድርግ፤ ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 20በሕይወት እንድትኖርና አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን ምድር እንድትወርስ፣ የጽድቅ ፍርድን ብቻ ተከተል።
ሌሎችን አማልክት ስለ ማምለክ
21ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በምትሠራው መሠዊያ አጠገብ የአሼራን ምስል የዕንጨት ዐምድ አታቁም#16፥21 ወይም፣ ለአሼራ ብለህ ምንም ዐይነት ዛፍ አትትከል።22አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠላውን ማምለኪያ ዐምድ ለአንተ አታቁም።

Currently Selected:

ዘዳግም 16: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ