የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መክብብ 12

12
1የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣
“ደስ አያሰኙኝም”
የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣
በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን ዐስብ።
2ፀሓይና ብርሃን፣
ጨረቃና ከዋክብት ሳይጨልሙ፣
ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፣
3ቤት ጠባቂዎች ሲርዱ፣
ብርቱዎች ሲጐብጡ፣
ጥቂት በመሆናቸው ፈጪታዎች ሲያቆሙ፣
በመስኮት የሚያዩትም ሲፈዝዙ፣
4ወደ አደባባይ የሚያወጡ በሮች ሲዘጉ፣
ወፍጮ ሟልጦ ድምፁ ሲላሽ፣
ሰው በወፍ ድምፅ ሲነሣ፣
ዝማሬው ሁሉ ሲዳከም፤
5ዳገት መውጣት ሲያርድ፣
መንገድም ሲያስፈራ፣
የአልሙን ዛፍ ሲያብብ፣
አንበጣም ራሱን ሲጐትት፣
ፍላጎት ሲጠፋ፤
በዚያም ጊዜ ሰው ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ይሄዳል፤
አልቃሾችም በአደባባዮች ይዞራሉ።
6የብር ሰንሰለት ሳይበጠስ፣
የወርቅ ሳሕንም ሳይሰበር፣
የውሃ መቅጃው በምንጩ አጠገብ ሳይከሰከስ፣
ወይም መንኰራኵሩ በውሃ ጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፣
7ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣
መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ አምላክ ሳይመለስ፣
ፈጣሪህን ዐስብ።
8ሰባኪው#12፥8 ወይም የጉባኤ መሪ እንዲሁም በ9 እና 10 “ከንቱ ከንቱ
ሁሉም ነገር ከንቱ ነው!” ይላል።
የነገሩ ፍጻሜ
9ሰባኪው ጥበበኛ ብቻ አልነበረም፤ ነገር ግን ለሕዝቡ ዕውቀትንም ያስተምር ነበር። እርሱም በጥልቅ ዐሰበ፤ ተመራመረም፤ ብዙ ምሳሌዎችንም በሥርዐት አዘጋጀ። 10ሰባኪው ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ተመራመረ፤ የጻፈውም ቅንና እውነት ነበረ።
11የጠቢባን ቃላት እንደ ሹል የከብት መንጃ ናቸው፤ የተሰበሰቡ አባባሎቹም እጅግ ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች ሲሆኑ፣ ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው። 12ልጄ ሆይ፤ ከዚህ ሁሉ በላይ በማንኛውም ነገር ተጠንቀቅ፤ አንዳችም አትጨምር።
ብዙ መጻሕፍትን መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ ብዙ ማጥናትም ሰውነትን ያደክማል።
13እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣
የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤
አምላክን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤
ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።
14መልካምም ይሁን ክፉ፣
ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣
ማንኛውንም ሥራ አምላክ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።

Currently Selected:

መክብብ 12: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ