ዘፀአት 12

12
የፋሲካ በዓል
12፥14-20 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥4-8ዘኍ 28፥16-25ዘዳ 16፥1-8
1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በግብጽ እንዲህ አላቸው፤ 2“ይህ ወር ለእናንተ የወር መጀመሪያ፣ የዓመቱም መጀመሪያ ይሁንላችሁ። 3ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህን ንገሩ፤ ይህ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ጠቦት ለቤተ ሰቡ፣ አንዳንድ ጠቦት ለአባቱ ቤት ያዘጋጅ። 4ማንኛውም ቤተ ሰብ ለአንድ ሙሉ ጠቦት ቍጥሩ አነስተኛ ከሆነ፣ በጎረቤት ያሉትን ሰዎች ቍጥር እስከ ቅርብ ከሆነው ጋራ መካፈል ይኖርበታል፤ እያንዳንዱ ሰው በሚበላው መጠንም ምን ያህል ጠቦት እንደሚያስፈልግ መወሰን ይኖርባችኋል። 5የምትመርጡት ጠቦት በግ ወይም ፍየል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነቀፋ የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት መሆን አለበት። 6ወሩ በገባ እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው። 7ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጕበን ይቀቡ። 8ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ከቂጣ ጋራ ይብሉት። 9ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት። 10ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል። 11ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ በዐጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።
12“እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን ዐልፋለሁ፤ ግብጽን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።
14“ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። 15ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበት ቂጣ ብሉ። በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በእነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ። 16በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል።
17“የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብጽ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት። 18ከመጀመሪያው ወር ከዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። 19ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ። 20እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ቂጣ ነው መብላት ያለባችሁ።”
21ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቶሎ ሄዳችሁ ለየቤተ ሰቦቻችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን በግ ዕረዱ። 22ከዚያም ጭብጥ የሂሶጵ ቅጠል በመውሰድ፣ በሳሕን ውስጥ ካለው ደም ነክራችሁ የየቤቶቻችሁን ጕበንና ግራ ቀኝ መቃኑን ቀቡ። ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ። 23እግዚአብሔር ግብጻውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጕበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያን ደጃፍ ዐልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታችሁ ገብቶ እንዳይገድላችሁ ይከለክለዋል።
24“እናንተም ሆነ ልጆቻችሁ ይህን መመሪያ ቋሚ ሥርዐት አድርጋችሁ ትታዘዛላችሁ። 25እግዚአብሔር እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ይህን ሥርዐት ጠብቁ። 26ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣ 27‘ግብጻውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብጽ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት ዐልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም። 28እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።
29እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ፣ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ እስካለው እስረኛ የበኵር ልጅ ድረስ ያለውንና የእንስሳቱን በኵሮች ሁሉ ቀሠፋቸው። 30ፈርዖን፣ ሹማምቱና የግብጽ ሕዝብ በሙሉ ሌሊቱን ከመኝታቸው ተነሡ፤ እነሆ በመላዪቱ ግብጽ ልቅሶና ዋይታ ነበር፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረምና።
ከግብጽ መውጣት
31ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ሌሊቱን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ተነሡ፤ እናንተና እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን አምልኩ፤ 32እንዳላችሁት የበግና የፍየል መንጋችሁን፣ የቀንድና የጋማ ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።”
33ግብጻውያን አገራቸውን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡላቸው እስራኤላውያንን አጣደፏቸው። “አለዚያማ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉ። 34ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሖ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ። 35እስራኤላውያን ሙሴ እንዳዘዛቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎች፣ እንደዚሁም ልብስ እንዲሰጧቸው ግብጻውያኑን ጠየቋቸው። 36እግዚአብሔር በግብጻውያን ፊት ለእስራኤላውያን ሞገስ ስለ ሰጣቸው፣ የጠየቋቸውን ሁሉ ሰጧቸው፤ ስለዚህ የግብጻውያንን ንብረት በዝብዘው ወሰዱ።
37እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ። ከሴቶቹና ከልጆቹ ሌላ፣ ስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ ወንዶች ነበሩ። 38ከእነርሱም ጋራ ቍጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ ዐብሯቸው ወጣ፤ እንዲሁም አያሌ የበግ፣ የፍየል፣ የጋማና የቀንድ ከብት መንጋ ይዘው ወጡ። 39ከግብጽ ይዘው ከወጡት ሊጥ ያልቦካ ቂጣ ጋገሩ፤ ሊጡ አልቦካም ነበር፤ ምክንያቱም ከግብጽ በጥድፊያ እንዲወጡ ስለተደረጉ፣ ለራሳቸው ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ አልነበራቸውም።
40እንግዲህ እስራኤላውያን በግብጽ#12፥40 ማሶሬቴክ ቅጅ እንዲሁ ሲል፣ ኦሪተ ሳምራውያንና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም በግብጽና በከነዓን ይላሉ። የኖሩበት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር። 41ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር ሰራዊት ሁሉ ግብጽን ለቅቆ ወጣ። 42እግዚአብሔር በዚያች ሌሊት እነርሱን ከግብጽ ለማውጣት ዘብ የቆመበት በመሆኑ፣ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፣ በዚያች ሌሊት እስራኤላውያን ሁሉ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።
የፋሲካ በዓል እንዴት መከበር እንዳለበት
43 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዐት እንዲህ ነው፤ ባዕድ የሆነ ሰው ከፋሲካው ምግብ አይብላ፤ 44በገንዘብ የገዛኸው ማንኛውም ባሪያ ከገረዝኸው በኋላ መብላት ይችላል፣ 45ነገር ግን ለጊዜው የተቀመጠ እንግዳና ቅጥር ሠራተኛ መብላት የለበትም።
46“ምግቡ በአንድ ቤት ውስጥ መበላት አለበት፤ ምንም ሥጋ ከቤት እንዳይወጣ፤ ምንም ዐጥንት እንዳትሰብሩ። 47የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በዓሉን ማክበር ይኖርበታል።
48“በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን የፋሲካ በዓል ማክበር ቢፈልግ፣ በቤተ ሰቡ ያሉት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው፤ ከዚያም እንደ ተወላጅ ተቈጥሮ የሥርዐቱ ተካፋይ ይሁን። ያልተገረዘ ወንድ ግን የፋሲካን ምግብ አይብላ። 49ይህም ሕግ በዜጋውም ሆነ በመካከላችሁ በሚኖሩት መጻተኞች ላይ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።”
50እስራኤላውያን በሙሉ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ። 51በዚያችው ዕለት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው አድርጎ ከግብጽ ምድር አወጣቸው።

Currently Selected:

ዘፀአት 12: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ