ዘፀአት 3

3
ሙሴና የሚንበለበለው ቍጥቋጦ
1አንድ ቀን ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቱን የዮቶር በጎችና ፍየሎች እየጠበቀ ሳለ፣ መንጋውን እየነዳ ወደ ምድረ በዳው ዳርቻ አምርቶ የእግዚአብሔር ተራራ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ኮሬብ ቀረበ። 2እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቍጥቋጦው ውስጥ በሚንቀለቀል የእሳት ነበልባል መካከል ተገለጠለት። ሙሴም ቍጥቋጦው በእሳት ቢያያዝም እንኳ፣ አለመቃጠሉን አየ። 3ሙሴም፣ “ቍጥቋጦው ለምን እንደማይቃጠል ቀረብ ብዬ ይህን አስገራሚ ነገር ልመልከት” አለ።
4ሙሴ ሁኔታውን ለመመልከት መቅረቡን እግዚአብሔር ባየ ጊዜ፣ ከቍጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር “ሙሴ፣ ሙሴ” ብሎ ጠራው።
ሙሴም “አቤት እነሆኝ” አለው።
5እግዚአብሔርም፣ “ወደዚህ እንዳትቀርብ፤ ይህች የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” አለው። 6ቀጥሎም፣ “እኔ የአባቶችህ የአብርሃም፣ የይሥሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” አለው። በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።
7ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “በግብጽ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቻለሁ። 8ስለዚህም ከግብጻውያን እጅ ልታደጋቸውና ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ሰፊና ለም ወደሆነችው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ላወጣቸው ወርጃለሁ። 9አሁንም የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደርሷል፤ ግብጻውያን የሚያደርሱባቸውን ግፍ አይቻለሁ። 10በል እንግዲህ ና፤ ሕዝቤን፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር እንድታወጣቸው ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ”።
11ሙሴ እግዚአብሔርን፣ “ወደ ፈርዖን የምሄድና የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” አለው።
12እግዚአብሔርም፣ “እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እኔ የላክሁህ ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቡን ከግብጽ ካወጣሃቸው በኋላ በዚህ ተራራ ላይ እግዚአብሔርን ታመልካላችሁ” አለው።
13ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ወደ እስራኤል ልጆች ሄጄ፣ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለው።
14እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ#3፥14 ወይም እኔ የምሆነው እኔኑ ነው ማለት ሊሆን ይችላል።፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው።
15ደግሞም እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር#3፥15 በዕብራይስጥ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ድምፅ በ14 ላይ፣ እኔ ነኝ ከሚለው ሐረግ ጋራ ተመሳሳይ ድምፅ አለው። ያህዌ የሚለውም የቃል ውልደት እኔ ነኝ ከሚለው ሐረግ ነው። ወደ እናንተ ልኮኛል፤’
“ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤
ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ
ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው።
16“ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብጽ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ። 17ስለዚህም በግብጽ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ’ ብሏል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
18“የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብጽ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጕዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ። 19የግብጽ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በቀር መቼም እንደማይለቅቃችሁ ዐውቃለሁ። 20ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቅቃችኋል።
21“ይህ ሕዝብ በግብጻውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም። 22እያንዳንዷ ዕብራዊት ከጎረቤቷም ይሁን ዐብራት ከምትኖረው ግብጻዊት የብርና የወርቅ ጌጣጌጦች እንደዚሁም ልብስ እንድትሰጣት ትጠይቅ። እነዚህንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታስጌጧቸዋላችሁ፤ ታለብሷቸዋላችሁም። በዚህም መንገድ የግብጻውያኑን ሀብት በእጃችሁ አግብታችሁ ትወጣላችሁ።”

Currently Selected:

ዘፀአት 3: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ