የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 27

27
ለጢሮስ የወጣ ሙሾ
1ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ጢሮስ ሙሾ አውርድ፤ 3በባሕር መግቢያ ላይ ለምትገኘውና በብዙ ጠረፎች ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋራ ለምትነግደው ለጢሮስ እንዲህ በላት፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ ‘ጢሮስ ሆይ፤
“ፍጹም ውብ ነኝ” ብለሻል፤
4ዳርቻሽ በባሕር መካከል ነው፤
ሠሪዎችሽም ፍጹም ውብ አድርገውሻል።
5ሳንቃዎችሽን ሁሉ፣
ከሳኔር#27፥5 ሄርሞንን ማለት ነው። በመጣ ጥድ ሠሩ፤
ደቀልንም ይሠሩልሽ ዘንድ፤
ከሊባኖስ ዝግባ አመጡ።
6ከባሳን በመጣ ወርካ፣
መቅዘፊያሽን ሠሩ፤
ከቆጵሮስ#27፥6 ዕብራይስጡ ኪጢም ይለዋል። ጠረፍ በመጣ ዝግባ፣#27፥6 በታርጕምም እንዲሁ ሲሆን የማሶሬቱ መጽሐፍ የድምፅ ተቀባዮች ፊደል አከፋፈል ግን የተለየ ነው።
በዝኆን ጥርስ ለብጠው ወለልሽን ሠሩ።
7የመርከቦችሽ ሸራ ጥልፍ ሥራ ያለበት የግብጽ በፍታ ነበረ፤
ይህም እንደ ዐርማ አገለገለሽ።
መጋረጃዎችሽ ከኤሊሳ ጠረፍ የመጡ፣
ባለሰማያዊና ሐምራዊ ቀለም ነበሩ።
8ቀዛፊዎችሽ ከሲዶናና ከአራድ የመጡ ነበሩ፤
ጢሮስ ሆይ፤ የራስሽ ጠቢባን የመርከቦችሽ መሪዎች ነበሩ።
9የጌባል ሽማግሌዎችና#27፥9 ባይብሎስ ማለት ነው። ባለሙያዎች፣
መርከብሽን ለመገጣጠም በመካከልሽ ነበሩ፤
የባሕር መርከቦችና መርከበኞቻቸው ሁሉ፣
ከአንቺ ጋራ ሊገበያዩ ይመጡ ነበር።
10“ ‘የፋርስ፣ የሉድና የፉጥ ሰዎች፣
ወታደር ሆነው በሰራዊትሽ ውስጥ አገለገሉ፤
ሞገስም ይሆኑሽ ዘንድ፣
ጋሻቸውንና የራስ ቍራቸውን በግድግዳሽ ላይ ሰቀሉ።
11የአራድና የሔሌክ ሰዎች፣
ቅጥርሽን በየአቅጣጫው ጠበቁ፤
የገማድ ሰዎችም፣ በምሽግሽ ውስጥ ነበሩ።
ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፤
ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ።
12“ ‘ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ፣ ተርሴስ ከአንቺ ጋራ የንግድ ልውውጥ ታደርግ ነበር፤ ብርና ብረት፣ ቈርቈሮና እርሳስ አምጥታ ሸቀጥሽን ትለውጥ ነበር።
13“ ‘ያዋን፣ ቶቤልና ሜሼኽ ከአንቺ ጋራ ይነግዱ ነበር፤ ባሪያዎችንና የናስ ዕቃዎችን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
14“ ‘የቤት ቶጋርማ ሰዎችም መጋዣዎችን፣ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን በሸቀጥሽ ለወጡ።
15“ ‘የድዳን#27፥15 ከሰብዐ ሊቃናት ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን ዕብራይስጡ ግን ዴዳን ይለዋል። ሰዎች ከአንቺ ጋራ ተገበያዩ፤ ብዙ የጠረፍ አገሮችም የንግድ ደንበኞችሽ ነበሩ፤ በዝኆን ጥርስና በዞጲ ሸቀጥሽን ይገዙ ነበር።
16“ ‘ምርትሽ ብዙ እንደ መሆኑ፣ ሶርያ#27፥16 በአብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆችም እንዲሁ ሲሆን፣ አንዳንድ የጥንት የዕብራይስጥ ቅጆችና ሱርስቱ ግን ኤዶም ይላሉ። ከአንቺ ጋራ ትገበያይ ነበር፤ ሸቀጥሽንም በበሉር፣ በሐምራዊ ጨርቅ፣ በወርቀ ዘቦ፣ በጥሩ በፍታ፣ በዛጐልና በቀይ ዕንቍ ይለውጡ ነበር።
17“ ‘ይሁዳና እስራኤል እንኳ ከአንቺ ጋራ ተገበያይተዋል፤ የሚኒትን ስንዴ፣ ጣፋጭ ቂጣ፣#27፥17 በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም። ማር፣ ዘይትና በለሳን በማምጣት በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
18“ ‘ከሀብት ከንብረትሽ ብዛት የተነሣ፣ ደማስቆ የኬልቦንን የወይን ጠጅና፣ የዛሐርን የበግ ጠጕር በማቅረብ ከአንቺ ጋራ ተገበያይታለች። 19ዌንዳንና ያዋን ከኦሴል መጥተው ከአንቺ ጋራ የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር፤ ቀልጦ የተሠራ ብረትን፣ ብርጕድንና ከሙንን በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
20“ ‘ድዳን ግላስ በማቅረብ ከአንቺ ጋራ ትነግድ ነበር።
21“ ‘የዐረብና የቄዳር መሳፍንት ሁሉ ደንበኞችሽ ነበሩ፤ ጠቦትና አውራ በግ፣ ፍየልም አምጥተው ከአንቺ ጋራ ይገበያዩ ነበር።
22“ ‘የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች ከአንቺ ጋራ ይገበያዩ ነበር፤ ምርጥ የሆነውን የሽቱ ቅመም ዐይነት ሁሉ፣ የከበረ ድንጋይና ወርቅ በማቅረብ በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።
23“ ‘ካራን፣ ካኔ፣ ዔድን፣ የሳባ ነጋዴዎች፣ አሦርና ኪልማድ ከአንቺ ጋራ የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር። 24እነዚህም በገበያሽ ውስጥ ያማረ ልብስ፣ ሰማያዊ ካባ፣ ወርቀ ዘቦ እንዲሁም በኅብረ ቀለም ያሸበረቀና በጥብቅ የተታታ ስጋጃ በማቅረብ ከአንቺ ጋራ ይነግዱ ነበር።
25“ ‘የተርሴስ መርከቦች፣
ሸቀጥሽን አጓጓዙልሽ፤
በባሕር መካከልም፣
በከባድ ጭነት ተሞልተሽ ነበር።
26ቀዛፊዎችሽ፣
ወደ ጥልቁ ባሕር ይወስዱሻል፤
የምሥራቁ ነፋስ ግን፣
በባሕሩ መካከል ይሰባብርሻል።
27የመርከብ አደጋ በሚደርስበሽ ቀን፣
ሀብትሽ፣ ሸቀጥሽና የንግድ ዕቃሽ፣
መርከብ ነጂዎችሽ፣ መርከበኞችሽና መርከብ ሠሪዎችሽ፣
ነጋዴዎችሽና ወታደሮችሽ ሁሉ፣
በመርከብ ላይ ያሉትም ሁሉ፣
ወደ ባሕሩ ወለል ይዘቅጣሉ።
28መርከበኞችሽ ሲጮኹ፣
የባሕሩ ጠረፍ ይናወጣል።
29ቀዛፊዎች ሁሉ፣
መርከባቸውን ጥለው ይሄዳሉ፤
መርከብ ነጂዎችና መርከበኞችም ሁሉ፣
ወርደው ባሕሩ ዳር ይቆማሉ፤
30ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣
በምሬት ያለቅሱልሻል፤
በራሳቸውም ላይ ዐቧራ ነስንሰው፣
በዐመድ ላይ ይንከባለላሉ።
31ስለ አንቺ ጠጕራቸውን ይላጫሉ፤
ማቅም ይለብሳሉ፤
በነፍስ ምሬት፣
በመራራም ሐዘን ያለቅሱልሻል።
32ስለ አንቺ በዋይታ ያለቅሳሉ፤
እንዲህም እያሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤
“ባሕር ውጦት የቀረ፣
እንደ ጢሮስ ማን አለ?”
33ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ፤
ብዙ ሕዝቦችን ታጠግቢ ነበር፣
በታላቅ ሀብትሽና ሸቀጥሽ፣
የምድርን ነገሥታት ታበለጥጊ ነበር።
34አሁን ግን በጥልቅ ውሃ ውስጥ፣
በባሕር ተንኰታኵተሻል፤
ጭነትሽና ተሳፋሪዎችሽ ሁሉ፣
ከአንቺ ጋራ ሰጥመዋል።
35በጠረፍ አገር የሚኖሩ ሁሉ፣
በአንቺ ሁኔታ ተደናገጡ፤
ንጉሦቻቸው በፍርሀት ራዱ፤
ፊታቸውም ተለዋወጠ።
36በሌሎች ሕዝቦች መካከል ያሉ ነጋዴዎች ምንኛ አፏጩብሽ!
መጨረሻሽ አስደንጋጭ ሆነ፤
ለዘላለምም አትገኚም።’ ”

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 27: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ