የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 33

33
ሕዝቅኤል ጕበኛው
1ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በምድር ላይ ሰይፍን ሳመጣ፣ የምድሪቱ ሕዝብ ከሰዎቻቸው አንዱን መርጠው ጕበኛ ቢያደርጉት፣ 3እርሱም በምድሪቱ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ቢነፋ፣ 4ከዚያም ማንም መለከቱን ሰምቶ ባይጠነቀቅ፣ ሰይፍም መጥቶ ሕይወቱን ቢያጠፋ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል። 5የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባለመጠንቀቁ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ግን ራሱን ባዳነ ነበር። 6ነገር ግን ጕበኛ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ሳይነፋ ቢቀርና ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት ሰይፍ ቢያጠፋ፣ ያ ሰው ስለ ኀጢአቱ ይወሰዳል፤ ጕበኛውን ግን ስለ ሰውየው ደም ተጠያቂ አደርገዋለሁ።’
7“የሰው ልጅ ሆይ፤ አንተን ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው። 8ኀጢአተኛውን፣ ‘አንተ ክፉ ሰው፤ በርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተን ግን ስለ ደሙ እጠይቅሃለሁ። 9ነገር ግን ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ አስጠንቅቀኸው ከመንገዱ ባይመለስ፣ እርሱ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ራስህን አድነሃል።
10“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘እንዲህ ትላላችሁ፤ “በደላችንና ኀጢአታችን ከብዶናል፤ ከዚህም#33፥10 ወይም በርሱ የተነሣ ልንጠፋ ነው፤ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን?” ’ 11እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ! ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ! የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’
12“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች እንዲህ በላቸው፤ ‘ጻድቅ ሰው ትእዛዝን በተላለፈ ጊዜ የቀድሞ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛ ሰው ከኀጢአቱ ከተመለሰ፣ ከቀድሞ ክፋቱ የተነሣ አይጠፋም። ጻድቅ ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ በቀድሞ ጽድቁ ምክንያት በሕይወት እንዲኖር አይደረግም።’ 13ጻድቁን ሰው በርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለው፣ እርሱም ጽድቁን ተማምኖ ክፋት ቢሠራ፣ ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ በኀጢአቱም ምክንያት ይሞታል። 14እንዲሁም ክፉውን ሰው፣ ‘በርግጥ ትሞታለህ’ ብለው፣ እርሱም ከኀጢአቱ ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ 15ለሰጠው ብድር የተቀበለውን መያዣ ቢመልስ፣ የሰረቀውንም መልሶ ቢሰጥ፣ ሕይወት የሚሰጡትን ትእዛዞች ቢከተል፣ ክፉ ነገርንም ባያደርግ፣ በርግጥ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ አይሞትምም። 16ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17“ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው። 18ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ክፉ ቢሠራ፣ ይሞትበታል። 19ክፉም ሰው ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል። 20ይሁን እንጂ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”
የኢየሩሳሌም መውደቅ
21በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐምስተኛው ቀን፣ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፣ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለኝ። 22ሰውየው ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት፣ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ላይ ነበረች፤ በማለዳም ሰውየው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ፤ ከዚያ በኋላ ዝም አላልሁም።
23ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 24“የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ። 25ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈስሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ? 26በሰይፋችሁ ትመካላችሁ፤ አስጸያፊ ነገሮችን ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት ታረክሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?’
27“እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተረፉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በገጠር ያሉትን ቦጫጭቀው እንዲበሏቸው ለዱር አራዊት እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽግና በዋሻ ያሉትም በቸነፈር ይሞታሉ። 28ምድሪቱን ጠፍና ባድማ አደርጋታለሁ፤ የምትመካበት ጕልበቷ እንዳልነበረ ይሆናል፤ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ። 29ካደረጓቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሣ፤ ምድሪቱን ጠፍና ባድማ በማደርግበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’
30“አንተን በሚመለከት፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ የአገርህ ሰዎች በየቤቱ በርና ግድግዳ ሥር ሆነው ስለ አንተ ይነጋገራሉ፤ እርስ በራሳቸውም እንዲህ ይባባላሉ፤ ‘ኑና ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት እንስማ።’ 31ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ሕዝቤ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህንም ለመስማት ከፊትህ ይቀመጣሉ፤ ነገር ግን አይፈጽሙትም። በከንፈራቸው ብዙ ፍቅርን ይገልጣሉ፤ ልባቸው ያረፈው ግን ተገቢ ባልሆነ ጥቅም ላይ ነው። 32ቃልህን ሰምተው ሥራ ላይ የማያውሉት በመሆናቸው፣ አንተ ለእነርሱ በአማረ ድምፅ የፍቅር ዘፈን የሚዘፍን፣ በዜማ መሣሪያም አሳምሮ የሚጫወት ሙዚቀኛ ሆነህላቸዋል።
33“ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ደግሞም በርግጥ ይሆናል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ፣ ያውቃሉ።”

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 33: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ