ዘፍጥረት 12

12
የአብራም መጠራት
1 እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ከአገርህ ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።
2“ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤
ደግሞም እባርክሃለሁ፤
ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤
ለሌሎች በረከት ትሆናለህ።
3የሚባርኩህን እባርካለሁ፤
የሚረግሙህን ረግማለሁ፤
የምድር ነገዶችም፣
በአንተ ይባረካሉ።”
4ስለዚህ አብራም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም ዐብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ሲወጣ ዕድሜው 75 ዓመት ነበረ። 5አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ሳሉ ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዘው በመጓዝ ከነዓን ምድር ገቡ።
6አብራም ትልቁ የሞሬ ዛፍ እስከሚገኝበት እስከ ሴኬም ድረስ በምድሪቱ ዘልቆ ሄደ። በዚያ ጊዜ ከነዓናውያን በዚሁ ምድር ይኖሩ ነበር። 7እግዚአብሔርም ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ።
8ከዚያም ተነሥቶ ከቤቴል በስተምሥራቅ ወዳሉት ተራሮች ሄደ፤ ቤቴልን በምዕራብ፣ ጋይን በምሥራቅ አድርጎ ድንኳን ተከለ፣ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ጸለየ።
9አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።
አብራም በግብጽ አገር
12፥10-20 ተጓ ምብ – ዘፍ 20፥1-1826፥1-11
10በዚያም ምድር ጽኑ ራብ ገብቶ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አብራም ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ ግብጽ ወረደ። 11ግብጽ ለመግባት ጥቂት ሲቀረው አብራም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ውብ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ 12ግብጻውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ፣ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ብለው እኔን ይገድላሉ፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13ስለዚህ ለአንቺ ሲሉ እንዲንከባከቡኝ፣ ሕይወቴም እንድትተርፍ፣ ‘እኅቱ ነኝ’ በዪ።”
14አብራም በግብጽ አገር እንደ ደረሰ ግብጻውያን፣ ሦራ እጅግ ውብ ሴት እንደ ሆነች አዩ፤ 15የፈርዖንም ሹማምት ባዩአት ጊዜ፣ ለፈርዖን አድንቀው ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ወሰዷት። 16በርሷም ምክንያት ፈርዖን አብራምን አክብሮ አስተናገደው፤ በጎችና ከብቶች፣ ተባዕትና እንስት አህዮች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችን ሰጠው።
17 እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተ ሰዎቹን በጽኑ ደዌ መታቸው። 18ከዚያም ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ‘ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርኸኝም?’ 19ለምን ‘እኅቴ ናት’ አልኸኝ? ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል አሁንም ሚስትህ ይህችው፤ ይዘሃት ሂድ!” 20ከዚያም ፈርዖን ስለ አብራም ለባለሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋራ አሰናበቱት።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 12: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ