ዘፍጥረት 13
13
የአብራምና የሎጥ መለያየት
1አብራም ሚስቱንና ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከግብጽ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም ዐብሮት ነበረ። 2አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር።
3አብራም ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳኑን ከተከለበት፣ 4ለመጀመሪያ ጊዜም መሠዊያ ካቆመበት ስፍራ ደረሰ፤ በዚያም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።
5ከአብራም ጋራ ዐብሮት ይጓዝ የነበረው ሎጥ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት። 6ሆኖም ሁለቱ አንድ ላይ ሲኖሩ ስፍራው አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ ዐብረው መኖር አልቻሉም። 7ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ መንጎች እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያ ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር።
8አብራምም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማቾች ነንና፣ በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም። 9ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።”
10ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብጽ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው። 11ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ ወደ ምሥራቅ አመራ፤ ሁለቱ ሰዎች በዚሁ ተለያዩ። 12አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ። 13የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ።
14ሎጥ ከተለየው በኋላ እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤ 15ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ። 16ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ ማንም የምድርን ትቢያ ሊቈጥር እንደማይችል ሁሉ የአንተም ዘር የማይቈጠር ይሆናል። 17እንግዲህ ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።”
18አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ ሄዶም ኬብሮን በሚገኙት ትልልቅ የመምሬ ዛፎች አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.