ዘፍጥረት 16

16
አጋርና እስማኤል
1የአብራም ሚስት ሦራ፣ ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤ እርሷም አጋር የምትባል ግብጻዊት አገልጋይ ነበረቻት። 2አብራምንም፣ “እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ አድርጎኛል። ምናልባት በርሷ በኩል ልጆች አገኝ እንደሆን ሄደህ ከአገልጋዬ ጋራ ተኛ” አለችው።
አብራምም ሦራ ባለችው ተስማማ። 3አብራም በከነዓን ምድር ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ሚስቱ ሦራ ግብጻዊት አገልጋይዋን አጋርን ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ሰጠችው። 4አብራምም ከአጋር ጋራ ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች።
አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች። 5ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው።
6አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደ ሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች።
7እግዚአብሔር መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር። 8መልአኩም፣ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፤ ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት።
እርሷም፣ “ከእመቤቴ ከሦራ ኰብልዬ መምጣቴ ነው” ብላ መለሰች።
9እግዚአብሔርም መልአክ፣ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለርሷም ተገዥላት” አላት። 10ደግሞም የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር አይችልም” አላት።
11እግዚአብሔርም መልአክ በተጨማሪ እንዲህ አላት፤
“እነሆ፤ ፀንሰሻል፤
ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤
እግዚአብሔር ችግርሽን ተመልክቷል፤
ስሙን እስማኤል#16፥11 እስማኤል ማለት እግዚአብሔር ይሰማል ማለት ነው። ትዪዋለሽ።
12እርሱም እንደ ዱር አህያ ይሆናል፤
እጁንም ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ ያነሣል፤
ያገኘውም ሁሉ እጁን ያነሣበታል፤
ከወንድሞቹ ሁሉ ጋራ እንደ ተጣላ ይኖራል።”#16፥12 ወይም በስተምሥራቅ ይኖራል
13እርሷም ያናገራትን እግዚአብሔርን፣ “ኤልሮኢ” ብላ ጠራችው፤ ምክንያቱም “የሚያየኝን አሁን አየሁት”#16፥13 ወይም ኋላውን አየሁት ብላ ነበርና። 14ከዚህ የተነሣ የዚያ ምንጭ ስም፣ “ብኤርላሃይሮኢ”#16፥14 ብኤርላሃይሮኢ ማለት የሚያየኝ የሕያው ምንጭ ማለት ነው። ተብሎ ተጠራ፤ እስካሁንም በቃዴስና በባሬድ መካከል ይገኛል።
15አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም ስሙን እስማኤል ብሎ ጠራው። 16አብራም፣ አጋር እስማኤልን በወለደች ጊዜ ዕድሜው 86 ዓመት ነበር።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 16: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ